ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ ጥሪ አቀረበች
###########################
ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2029 ወይም 2031 ለማዘጋጀት ለዓለም አትሌቲክስ ጥሪ አቅርባለች።
ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ፍላጎት ላላቸው ሃገራት በቶኪዮ በተዘጋጀው የኦብዘርቨር መርሃግብር ላይ ከመንግስትና ከፌዴሬሽኑ የተወጣጡ አመራሮች የተካፈሉ ሲሆን ልምድና ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበተል።
መንግስት ለአትሌቲክሱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ግብአቶች በሟሟላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ችግሮችን በመቅረፍ እና በቂ ስታዲየሞች በመገንባት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ መክዩ መሐመድ ተናግረዋል
ሚኒስትሩ አክለውም አትሌቲክሱ ላይ ሰፊ ስራ በመስራት ወደ ነበረው ከፍታ እና መነቃቃት ማድረስም እንደሚገባም አንስተዋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩላቸው አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙት የስፖርት ፋሲሊቲዎችና ማዘውተሪያ፣ ሆቴሎች፣ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት እና ሌሎች ለሻምፒዮናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ካዘጋጁ አገራት ያላቸውን ልምድ ለመካፈል በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እየተሳተፉ ያሉት የፌዴሬሽኑ አመራሮች በቶኪዮ ዓለም አቀፍ ስቴዲየም በመዘዋወር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ልምድ ልውውጥና ተሞክሮ አድርገዋል።