የካቲት 27/2010 ዓ. ም፣ አ/አ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ፤

ከየካቲት 22 – 25/2010 ዓ. ም. በእንግሊዝ –  በርሚንግሃም ከተማ ሲካሄድ በነበረው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍሎ በ4 ወርቅና በ1 ብር ሜዳልያ ከአለም 2ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ሆኖ ላጠናቀቀው ቡድናችን ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 27/2010 ዓ. ም. ማለዳ 12፡35 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በአቀባበል ሥነ ስርአቱ ላይ የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚ/ር ሚኒስትር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ም/ፕሬዝዳንት አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከልዩ ልዩ ተቋማት ተወክለው የተገኙ የሥራ ኃላፊዎችና የሚዲያ ተቋማት በተገኙበት ለልኡካን ቡድኑ አባላት የአበባ ጉንጉን ተበርክቷል፡፡

በሥነ ስርአቱ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ንግግር ያደረገ ሲሆን በተሳታፊ ብዛት ሌሎች ሃገራት የተሻሉ ሆነው ቢገኙም በጥቂት አትሌቶች በርካታ ሚዳልያዎች ማስመዝገብ መቻላችን ትልቅ ስኬት ቢሆንም አያኩራራንም፤ በመሆኑም ከዚህ በተሻለ ተሳትፎና ውጤት በአለም አደባባይ ላይ ልንታይ ይገባናል በማለት አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ክቡር ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ በጣም በርካታ አለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች ያሉን በመሆናቸው ከወዲሁ በጠንካራ ዝግጅት ለተሻለ ውጤት መብቃት እንደሚገባና የተጀመረው መነሳሳት ሊቀጥል እንደሚገባው፣ በተጨማሪም የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከፊታችን የሚጠብቀን በመሆኑ ታናናሾቻችሁን በመምከርና አቅጣጫ በማሳየት የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው የኢፌዲሪ ወ/ስ/ሚ/ር ሚኒስትር ባሰሙት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ኮርታችሁ ያኮራችሁን አትሌቶቻችን ነገም ከዚያ ወዲም እንደመንግስት ከጎናችሁ መሆናችንን መግለጽ እወዳለሁ በማለት አስታውቀዋል፡፡

የአቀባበል ፕሮግራሙም በጋራ የፎቶ ሥነ ስርአት ተጠናቋል፡፡

Similar Posts
Latest Posts from