ጀግናዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በመወከል ትወዳደራለች።

##########################

ጀግናዋ የፓሪስ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ እና የለንደን ማራቶን (Women’s only World Record) አሸናፊዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በመወከል ትወዳደራለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአሠልጣኟ ጋር ባደረገው ስኬታማ እና ውጤታማ ውይይት ጀግናዋ አትሌት ትዕግስት በዓለም ሻምፒዮና ላይ ሀገርዋን እና ህዝቧን በመወከል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ በጃፓን ቶኪዮ ላይ ለማውለብለብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ።

በተደረገው ውይይት ላይም “ከሀገርና ከህዝብ ምንም የሚበልጥ ነገር የለም” በማለት በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ እና ፌዴሬሽኑ ያቀረበላት የአገር ጥሪ በፀጋ እንደምትቀበል አሰልጣኝዋ ገልፀዋል ።

የጀግናዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ መጀመሪያ “በርሊን ማራቶን” ለመሮጥ የቀረበ ጥያቄ “በኬንያዊቷ አትሌት ሩት” የተያዘውን ክብረወሰን ለመመለስ እና በአሁኑ ስዓት አትሌቷ በጥሩ አቋም ላይ በመሆኗ ክብረወሰን ቢሻሻል የኢትዮጵያ ስም ከፍ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ትዕግስት ያሳየችውን ታላቅ የሀገር ፍቅርና፣ ሀገርና ህዝብ በማስቀደም በጃፓን ቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና ላይ ተሳታፊ እንድትሆን የቀረበላት ጥያቄ በጎ ምላሽ በመስጠቷ አክብሮትና ምስጋና አቅርቧል ።

ከአትሌቷ በተጨማሪም አሠልጣኟ ለሀገር እንድትሮጥ ያሳዩት ፍላጎት ፌዴሬሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል ።

Loading

Categories: Uncategorized