ለ13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድምቀት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በድሬዳዋ ከተማ የ13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከግንቦት 18-24/2017 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል ፡፡
በሻምፒዮናው ላይ 8 ክልሎች ፣ 2 ከተማ አስተዳደሮች እና 35 ክለቦች እና ተቋማት በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ሲሆን ሻምፒዮናም በሁለት የእድሜ ምድብ ይካሄዳል ።
ከ20 ዓመት በታች 359 ሴቶች 463 ወንዶች በድምሩ 825 አትሌቶች እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች 178 ሴቶች 192 ወንዶች በድምር 370 በሁለቱም የእድሜ ምድብ በአጠቃላይ 1,195 አትሌቶች እንደሚወዳደሩ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁመዋል ።
የሻምፒዮናው አላማም እ.ኤ.አ ከጁላይ 16-20/2025 በናይጄሪያ አቡኩታ ከተማ ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ እንደሆነ ተነስቷል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፣የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ፣ የፌዴሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሐሪ ነጋሽ እና የፌዴሬሽኑ የህክምና ከፍተኛ ባሉሙያ ወይዘሮ ቅድስት ታደሰ በጋራ በመሆን በሻምፒዮናው ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።




