ለማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ተደረገ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ለአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ፕሮጀክቶች፣ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች የስፖርት አልባሳት ድጋፍ ማድረግ ነው ::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዓመታዊ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አድርጓል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሙኒኬሽን ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ሌተናል ኮነሬል አትሌት የማነ ፀጋይ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ፋሲሊቲ ማህበራትና አትሌቶች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ በቀለ በጋራ በመሆን ሰልጣኞች ፣ አሰልጣኞች እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የስፖርት ትጥቁን አስረክበዋል ።
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ቢኒያም ምሩፅ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍና ምልከታው ቀጣይነት ያለው መሆኑን አንስተው ፣ማዕከሉ በአገራችን ካሉት ግንባር ቀደምና ዉጤታማ ማዕከል መሆኑና በተለያዩ አህጉራዊና ዓለምአቀፍ ዉድድሮች የተሳተፉ አትሌት አባዲ ሀዲስ ፣አትሌት ፀጋዬ ኪዳኔ፣አትሌት ፎቴን ተስፋይ ፣አትሌት ፅጌ ገ/ ሰላማ እና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ያፈራ ማዕከል መሆኑን በመጠቆም ፌዴሬሽኑ አስፈላጊ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ አሳስበዋል ።
የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ሌተናል ኮነሬል አትሌት የማነ ፀጋይ በበኩላቸው ማዕከሉ በጣም በርካታ ጀግኖች አትሌቶች ያፈራ መሆኑን አንስቶ ማዕከሉን ለማሳደግ በሚደረግ ሁለንተናዊ ጥረት እንደ ፌዴሬሽንም እንደ አትሌቶች ማህበርም ያለሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ እና አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።
በርክክቡ ላይ የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ መብራት ሀፍቱ ፣የደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ፣የደቡባዊ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ወይዘሮ ጀሚላ አበቡ ፣የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳኔ ተ/ሃይማኖት ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ለተደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን የስፖርት ትጥቁን ተረክቧል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ትጥቅ ስርጭቱን አሁንም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ።




