አትሌት መሰረት ደፋር በአሜሪካ የፊታችን እሁድ ትሸለማለች።
#################
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሰረት ደፋር የፊታችን እሁድ የሚካሄደው
የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ሽልማት የሚበረክላት ሲሆን መርሀግብሩ ላይ ለመታደም አሜሪካ ገብታለች።
በመርሀግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የአሜሪካ ሴናተሮች፣ ከንቲባዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ።
በየአመቱ ስኬትንና የላቀ ስራ የሰሩ ልዩ ተሸላሚዎች ከስፖርት፣ ከኪነጥበብ፣ ከቢዝነስ ዘርፍ ተመርጠው ላደረጉት በጎ አስተዋፅኦ ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን ዘንድሮ በአትሌቲክሱ የኦሊምፒክ እና ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ አትሌት መሰረት ደፋር የምትሸለም ሲሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በአለም አደባባይ ስላውለበለበች ምስጋና ታገኛለች ።
አፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ እስካሁን ለአራት ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣የዲባባ ቤተሰብና አትሌት ስለሺ ስህን ፣አትሌት ትዕግስት አሰፋና አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ተሸላሚ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።