የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመት ውስጥ አካትቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ፣በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር ውስጥ ለሚገኙ 37 የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለሚገኙ ሰልጣኝ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ለክልሎቹ የስፖርት አመራሮች የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ያደርጋል።
በዚህም መሠረት በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ለሚገኙ ፕሮጀክት ሰልጣኞች የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሀመድ እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ዮናስ በትሩ ትጥቁን ተረክበው ለሰልጣኞቹ አስረክበዋል።
እንዲሁም የሀረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙራድ አብዲ እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አቃቤ ንዋይ ወ/ሮ ፎዚያ በክሪ ለክልሉ ሰልጣኞች የተላከውን ትጥቅ ተረክበው ለሰልጣኞቹ ያስረከቡ ሲሆን በተመሳሳይ የሱማሌ ክልል ፕሮጀክት ሰልጣኞችን ትጥቅ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መሀመድ መሀዲ እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አብዱልቃድር ሙመድ አብዲ የሰልጣኞች ትጥቅ ተረክበው ለአትሌቶቹ አስረክበዋል።
በሁለቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሩ ያለውን የአትሌቲክስ አጠቃላይ እንቅስቃሴን በተመለከተ እንዲሁም በፕሮጀክት ስልጠና ላይ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል፣ በስልጠና ሂደት፣ በማዘውተሪያ ስፍራ እንዲሁም አጠቃላይ አፈፃፀምን አስመልክቶ ግምገማና ውይይት ተደርጎ የስራ መመሪያና አቅጣጫ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የሀብት አሰባሰብ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ሳራ ሀሰን፣ ዶ/ር ኤፍራህ መሀመድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የህክምና ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት አቶ ዮሐንስ እንግዳና አቶ ግርማ ለማ በድሬደዋ፣ በሀረር እና ጂግጅጋ ከተሞች በአካል በመገኘት የስፖርት አልባሳቱን ለሰልጣኞች፣ አሰልጣኞችና አመራሮች ያስረከቡ ሲሆን በተጨማሪም የክልሎቹን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ገምግመዋል።
በመጨረሻም ለሁሉም ክልሎች የስፖርት አመራሮች የቀጣይ አቅጣጫና የስራ መመሪያ በወ/ሮ ሳራ ሀሰን ተሰጥቷል።
ፌዴሬሽኑ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉን አሁኑም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ።



