የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከዓለም አትሌቲክስ ኤ.አይ.ዩ ጋር በመተባበር በወቅታዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጉዳይ ከአትሌቶች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል ።

መጋቢት 26/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከዓለም አትሌቲክስ ኤ.ኤይ.ዩ ጋር በመተባበር በወቅታዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጉዳይ ከአትሌቶች ፣ከአሰልጣኞች እና ማኔጀሮች ጋር ውጤታማ ውይይት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አካሂዷል ።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ በአሁኑ ስዓት በዓለማችን ትልቁ የአትሌቲክሱ አጀንዳ ከሆኑ መካከል አንዱ “አበረታች ቅመሞች” መሆኑን አንስቶ፣ ፌዴሬሽኑ በመከላከሉ ረገድ የተለያየ ስራ እየተገበረ እንደሆነ እና አትሌቶቻችንም ለምርመራ ፍቃደኛ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል ።

ፕሬዝዳንቱ ጨምሮ” የምርመራ ማዕከል” በኢትዮጵያ እንዲኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል አትሌቶቹ በምርመራ ወቅት አለመገኘት፣ የቤተሰብ ጣልቃገብነት ችግር፣ የመገኛ አድራሻ በትክክል አለመሙላት እና ሌሎች ችግሮች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ያብራሩ ሲሆን ተቋማቸው ከፌዴሬሽኑ ጋር በትብብር እና በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢ.አ.ፌ. ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን፣ የኢ.አ.ፌ. የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ይፍሩ እና የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ወይዘሮ ቅድስት ታደሰ ወቅታዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጉዳይ በጋራ የውይይት ሰነድ አቅርበዋል ።

የኔትወርክ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር፣ ለምርመራ የሚመጡ ባለሙያዎች ለአትሌት የሚያቀርቡት ጥያቄ አግባብ፣ የአድራሻ መገኛ፣ የቋንቋ ችግር፣ የባለሙያዎች የሙያ ችግር በተለይ በደም አወሳሰድ፣ የቻይና ውጤት አለመያዝ እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ከአትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና ማኔጀሮች በስፋት ተነስተዋል።

በመጨረሻም ለተነሱት ጥያቄዎች በዓለም አትሌቲክስ የኤ.አይ.ዩ ተወካይ ሚስተር ራፋኤል፣ በፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን እና በኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሣልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደረሳል ምላሽና ማብራሪያ የተሰጡ ሲሆን፣ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ስብሰባው ተጠናቋዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሣልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ፣ የዓለም አትሌቲክስ ኤ.አይ.ዩ ተወካይ ራፋኤል ሮክስ፣የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር አመራሮች ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Categories: Uncategorized