ጥቅምት 24 /2018 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኦሮሚያ ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ይህም ስምምነት የፌዴሬሽኑን ዲጂታላይዜሽን እና የማርኬቲንግ ስትራቴጂ አቅም የሚያሳድግ እንደሆነ የታመነበት ነው፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ ኦሮሚያ ባንክ የሀገራችን አትሌቲክስ ለመደገፍ ያከናወናቸዉን ተግባራት አድንቀዉ በቀጣይም ባንኩ ከፌዴሬሽኑ ጎን በመሆን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የሁለቱ የተቋማት ትብብር የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ እና የኦሮሚያ ባንክ ኢትዮጵያ በቀጣይ የዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት በምታደርገው እንቅስቃሴ ባንኩ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል ።

በተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሀብት አሰባሰብ እና ስፖንሰርሺፕ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አፅንኦት ሰጥተዋል ።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አትሌቲክሱን ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግና ፌዴሬሽኑ በሚያከናውናቸው ውድድሮች ባንኩ ይበልጥ ምርትና አገልግሎት ለማስተዋወቅ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል ።

የኦሮሚያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጆቴ ቀናቴ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር መስራት ትልቅ የአገር ኩራት ነው ብለዋል።

ከፌዴሬሽኑ ጋር ላለፋት 3 ዓመታት በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ስትራቴጂክ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግሯል ።

አቶ ጆቴ አያይዘውም ባንኩ ፌዴሬሽኑ በጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም እንዲሳካ በዲጂታላይዜሽን ተግባር እንደሚደግፉ ያነሱ ሲሆን፣
ኦሮሚያ ባንክ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመስራቱ ውጤታማ እንደሆነም አንስቷል ።

ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የገቢ አማራጮቹን ለማስፋት መሰል ስምምነቶችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመፈፀም ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ።

Categories: ዜና