ኢትዮጵያን ወክሎ በአሜሪካ ፍሎሪዳ በሚካሄደው 46ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን ሽኝት ተደርጎለታል ።

ክቡር መኪዩ መሐመድ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፣ ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት፣አሰልጣኞች፣የሚድያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።

ክቡር መኪዩ መሐመድ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አትሌቲክስ የሀገራችን መለያ በመሆኑ ሀገርን ወክላችሁ ስትሄዱ ኢትዮጵያን አሸናፊነት በሚያደርግ ሁሉ መስዋትነት መክፈል ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከልዑካን ቡድኑ ውጤት እንደሚጠብቅ ያስታወሱት ክቡር መኪዩ ሀላፊነት ወስዳችሁ በድል እንዲትመለሱ ተባብሮ መስራትን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

መንግስት በስፖርት ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ውድድርን ከማሸናፍም ባሻገር ኢትዮጵያን ገፅታ ለአለም ማስተዋወቅ በመሆኑ አትሌቶች ድርብ ሀላፊነት እንዳለባቸውም የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን የቪዛ ችግርን ለመቅረፍ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልፀው ቡድኑ ባይሟላም በጥሩ መንፈስ ለመጓዝ ዝግጅት እንዳደረገ ገልፀዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ችግሩን ለመፍታት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጎን በመሆን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ልዑክ ቡድኑን በመምራት ወደ ፍሎሪዳ የሚያቀኑት ወ/ሮ ሳራ ሀሰን በበኩላቸው በአንድነትና በትብብር በመስራት ” ኢትዮጵያ ታሸንፋለች” የሚለውን መርህ በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተጨማሪም ወይዘሮ ሳራ በፍቅር ፣በአንድነት ቡድኑ መስራቱን አንስተው ፣የኢትዮጵያ ህዝብ በፀሎት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል ።

የቡድኑ የቴክኒክ ቡድን መሪ አቶ ብስራት ለጥይበሉ ልዑኩ በጃንሜዳ፣በአደይአበባ ዓለምአቀፍ ስቴዲየም ፣በእንጦጦ እና በሌሎች ልምምዳቸውን መስራታቸውን አስገንዝቦ ፣ስለ አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅት አብራርቷል ።

ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ አሰልጣኞችን በመወከል ሲናገሩ በጋራ እቅድ አውጥተን አትሌቶች በአንድነት እንዲሰሩና የቀድሞ ውጤት እንዲመጣ ጥረት አድርገናል ብለዋል።

የአትሌቶች ተወካዮች አትሌት ታደሰ ወርቁ እና አትሌት ሂሩት መሸሻ በበኩላቸው የተሻለ ውጤት ለማምጣት በአንድነት ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በአሜሪካ ፍሎሪዳ የሚካሄደው 46ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ይጀምራል።

Categories: Uncategorized