የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌቲክስ አሰልጣኞችና ባለሙያዎች ጋር ውጤታማ ውይይት አካሄደ ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን “ከአትሌቲክስ አሰልጣኞች እና ባለሞያዎች” ጋር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ “በአትሌቲክስ አሰልጣኞች ደረጃ መስጫ፣መወዳደሪያ ማብራሪያ እና በብሄራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞች ምርጫ መመሪያ ” ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አድርጓል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣የአትሌቲክስ
አሰልጣኞች እና ባለሞያዎች እስከ አሁን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያመሰጉ ሲሆን፣እንደዚህ ዓይነት ውይይቶች “ለአትሌቲክሱ እድገት” ጉልህ ሚና እንዳላቸውና ቀጣይነት እንደሚኖረው በመክፈቻው ላይ ተናግሯል ።
የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በበኩላቸው አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የውይይት መድረኩ ማዘጋጀቱን አመስግነው ፣አሰልጣኞች “የአትሌቲክስ ቁልፍ ናቸዉ ” ፣አሁን ላይ ፌዴሬሽኑን በመምራት ላይ ያላችሁ በአትሌቲክስ ሂወት ያለፋችሁ በመሆናቹ ፣የአትሌቱ እና የአሰልጣኞች ችግር ትፈታላችሁ በማለት እንደዚህ ዓይነት ውይይቶች ለአትሌቲክሱ እድገት ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል ።
የፌዴሬሽኑ ስልጠና፣ጥናትና ምርምር ዳይሬክር ኢንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ የአትሌቲክስ አሰልጣኞች ደረጃ መስጫ እና የመወዳደሪያ ማብራሪያ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የአትሌቲክስ ስፖርት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አትሌቶች በሀገር ውስጥና በአለምአቀፍ ስልጠና ውድድሮች ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ ፣ተተኪዎች በጥራትና በብዛት ማፍራት የሚችሉ አሰልጣኞች በየደረጃቸው በመለየት ወጥነት ያለው አሰራርን ለማስፈን ዓላማ ያደረገ መሆኑ አንስተዋል ።
የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞች ምርጫ መመሪያ ሲያቀርቡ ዓላማው ኢትዮጵያን ወክለው በአህጉር ፣በአለምአቀፍ እንዲሁም በኦሎምፒክ ውድድር ላይ የሚሳተፉ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶችና አሰልጣኞችን ግልፅ ፣ፍትሀዊና ተጠያቂነት ባካተተ ስርዓት በመምረጥ ውጤታማ የሆኑ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች እና አሰልጣኞችን ማፍራት እንደሆነ አብራርተዋል ።
የቀረበ ሰነድ የሚበረታታ መሆኑን አሰልጣኞቹ ያነሱት ሲሆን ፣አትሌቶችና አሰልጣኞች የመፍራት አዝማሚያዎች ፣ክለቦች ሲፈርሱ ዝም ብሎ መመልከት፣ድጋፍ እና ክትትል ማነስ ፣ሴት አሰልጣኞች መብት በበቂ ሁኔታ አለማክበር ፣የአሰልጣኝ እና አትሌት ሽልማት እኩልነት ፣ልምድና ውጤት ያላቸውን አሰልጣኞች ትኩረት አለማድረግ፣የትራክ ከፍተኛ ችግር ፣በአትሌቶች ውድድር መምረጫ ግልፀኝነት ማነስ ፣እና ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ያገለገሉ አሰልጣኞች ተገቢ ክብር አለመስጠት፣የሚስተዋሉ የፌዴሬሽኑ ችግሮች መሆናቸው አሰልጣኞች በስፋት ጠይቀዋል ።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሰረት ደፋር በማጠቃለያው ፣እኛ እዚ እንድንደርስ “የአሰልጣኞች “ሚና ከፍተኛ መሆኑንና በተለይ በሴት አሰልጣኞች ማብቃት፣መደገፍና ላይ አበክረው እንደሚሰሩና የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራ ችግርም እንዲቀረፍ በትኩረት እንደሚሰሩ አንስተዋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣የተነሱት ፍሬያማ ሀሳቦችን በግብአትነት እንደሚጠቀሙና ፣ፌዴሬሽኑ ያወጣውን የመምረጫ መስፈርት ከአለም ሻምፒዮና ብኃላ ለመጠቀም እንደታሰበ ፣ተቀራርቦ ለመስራት ስራ አስፈጻሚው ዝግጁ መሆኑን ፣አገርንና አትሌቲክሳችን ማስቀደም እንደሚገባ ተናግሯል ።




