ለተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ተደረገ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ለአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ፕሮጀክቶች፣ ለክልል እና ለከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች የስፖርት አልባሳት ድጋፍ ማድረግ ነው ::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዓመታዊ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አድርጓል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባልና አቃቢ ንዋይ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባልና የቅሬታና የዲስፕሊን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ትዛዙ ሞሴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብስራት ለጥይበሉ በጋራ በመሆን የስፖርት ትጥቁን አስረክበዋል ።
የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በርካታ በአህጉራዊ እና ዓለምአቀፍ ውድድሮች የተሳተፉ አትሌቶች ያፈራ ማዕከል መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ አትሌት ሰው መሆን አንተነህ ፣አትሌት አቤል በቀለ፣ አትሌት ትነበብ አስረስ እና አትሌት ፅዮን አበበ እና ሌሎች ጀግኖች አትሌቶች ከመአከሉ የፈሩ አትሌቶች ናቸውም ብለዋል ።
በቀጣይም መአከሉ ጠንክሮ በመስራት ብዙ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ዶ/ር ትዕዛዙ ሞሴ በበኩላቸው ማእከሉ ለሚሰራው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማመስገን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተተኪ አትሌቶች ላይ ለመስራት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ከነዚህም አንዱ ማዕከላትን መከታተል እና መደገፍ ነው መሆኑን አንስተዋል ።
አቶ ብስራት በቀጣይም ከዚህ የተሻለ ውጤታማ ለመሆን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል ።
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚዎቹ ከውሎ ዩኒቨርስቲ አመራሮች፣ ከማእከሉ አሰልጣኞች እና አትሌቶች ጋር በጋራ የተወያዩ ሲሆን ማዕከሉን ለማጠናከር ፌዴሬሽኑ ድጋፍና ክትትሉ እንደሚቀጥልም በርክክቡ ላይ ተናግረዋል ።
በውይይቱም ላይ በአትሌቶች በኩል የትራክ እና የስልጠና መስሪያ መሳሪያዎች ዋና ችግሮች እንደሆኑባቸው በስፋት ያነሱ ሲሆን፣ስራ አስፈፃሚዎቹም ትራክ እንድሰራላቸው ዩኒቨርሲቲውን ጠይቀዋል ።
የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ስራአስኪያጅ አቶ መሀመድ አለባቸው ፣ የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ተወካይ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሳ አዳል ፣ የስፖርት ሳይንስ ት/ት ክፍል ዲን ዶ/ር ከፍያለው ዘነበ፣ ፌዴሬሽኑ ላደረገው ድጋፍ በማመስገን የስፖርት ትጥቁን ተረክቧል ።
በተያያዘ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚዎች እንድሁም የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ በዴሴ ከተማ አስተዳደር ያለውን የፕሮጀክት ጣቢያ እንዲሁም የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከል ሰልጣኝ አትሌቶችን በስልጠና ቦታ ላይ በመገኘት ጎብኝተዋል።
ከደሴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው፣ ከአትሌቶችና አሰልጣኞች ጋር በመወያየት አበረታተዋል ።
በመጨረሻም ስራ አስፈፃሚዎቹ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የወጣቶች እና ስፖርት ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ ጋር በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ትጥቅ ስርጭቱን አሁንም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ።



