ኢትዮጵያዊያዊያን ጀግኖች አትሌቶች የደመቁበት ለንደን ማራቶን !

በ46ኛው የለንደን ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ታሪካዊ ውጤት በማስመዝገብ ደማቅ ታሪክ ፅፏል።

በሴቶች የፓሪስ ኦሎምፒክ እና የቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ባለቤት ጀግናዋ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ለንደን ማራቶን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ ስታሸንፍ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰንም አስመዝግባለች።

አትሌት ትግስት አሰፋ በራሷ ተይዞ የነበረውን የሴቶች ብቻ የማራቶን የአለም ክብረወሰን 2:15:50 በ9 ሰከንድ በማሻሻል የለንደን ማራቶንን በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ አሸንፋለች።

በለንደን ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደረው ጀግናው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባት የቻለ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኗል።

ዮሚፍ ቀጀልቻ በውድድሩ 2ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የገባበት 1:59:41 የኢትዮጵያ አዲስ ክብረ ወሰን ነው ።

ከዚህ ቀደም በርቀቱ ፈጣን ሰአት ያስመዘገበው ጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን፤ በ2019 በርሊን ማራቶን ላይ 2:01:41 የተያዘ ነበር።

አትሌት ታምራት ቶላ 5ኛ ፣አትሌት ደሬሳ ገለታ 6ኛ እና አትሌት አዲሱ ጎበና 7ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል ።

Categories: Uncategorized