55ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን ማክሰኞ ይጀመራል

#########################################

መጋቢት12/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ55ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በ29ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ተሰጥቷል ።

ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት፣ ለአትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር ፣ አትሌቶችን በሽልማት ለማበረታታት ዓላማ ያደረገው በጉጉት የሚጠበቀው 55ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጋቢት15-20/ 2018 ዓ.ም በአደይ አበባ ዓለምአቀፍ ስቴዲየም ይካሄዳል ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ተናግሯል ።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቁና ዋነኛው ሀገራዊ የውድድር መድረክ የሆነው ይህ ውድድር 36 ክለቦችና ተቋማት እና 9 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን 436 ሴት፣ 621 ወንድ በድምሩ 1057 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ የፌዴሬሽኑ የውድድር እና ተሳትፎ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ጊዜ አድነው በመግለጫው ላይ ያብራሩ ሲሆን፣ ውድድሩን የሚመሩ ብቁ ባለሙያዎች መመደባቸው እና ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ ማስኬጃ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንደመደበ አብራርተዋል ።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአትሌቲክስ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የተነገረለት እና ዓለም የደረሰበትን የአትሌቲክስ ጉዞ በቴክኖሎጂ እና ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ የሚያደርግበት 29 መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በወሩ መጨረሻ እንደሚካሄድ ዛሬ ለሚዲያ አካላት ይፋ ሆኗል።

በጉባኤው ላይ 28ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤን ጨምሮ የ2017 በጀት አመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የ2017 በጀት አመት የውጭ ኦዲት ሪፖርት ፣የ2018 በጀት አመት የሥራ እቅድ አፈፃፀም በአጀንዳነት እንደሚቀርቡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን አስታውቀዋል።

በዘንድሮ ጉባዔ ተቋሙ ከዘመኑ ጋር ሊያራምደው የሚያስችለው ተቋማዊ ሪፎርምና አደረጃጀትን በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ምሁራን የተሰራውን ሪፎርም ሰነድ በጉባዔው የሚፀድቅ መሆኑም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል ።

በሌላ መልኩ የተከለሰው የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ እና ከተቋማዊ ሪፎርሙና ከስትራቴጂክ እቅድ በመነሳት መተዳደሪያ ደንቡንና ልዩ ልዩ መመሪያዎች በጉባኤ ቀርበው የሚፀድቁበት ጉባኤ እንደሚሆን ተመላክቷል።

ጉባኤው መጋቢት 26-27/2018 ዓ.ም በቢሸፍቱ ከተማ ላይ ይደረጋል ።

Categories: Uncategorized