ለቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈጻሚዎች የምስጋና እንዲሁም ለአዲሱ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚዎች የትውውቅ መርኃ-ግብር ተካሄደ።

************************

ታኅሣሥ 19/2017ዓ.ም

ለቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈጻሚዎች የምስጋና እንዲሁም ለአዲሱ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚዎች የትውውቅና የመልካም ምኞት መግለጫ መርኃ-ግብር ተካሂዷል።

በመርኃ-ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሸዊት ሻንካ፦ ፌዴሬሽኑን ላለፉት ዓመታት የመራችሁና የስራ ዘመናችሁን የጨርሳችሁ አመራሮች ህዝብ የሰጣችሁን አደራ በመቀበል በአትሌቲክስ ስፖርት ልማት ባደረጋችሁት ጥረት ለበርካታ አትሌቶች ስኬት እና እድገት ብሎም በዓለም አደባባይ የአገርን ገጽታ በመገንባትና የማህበረሰቡን ስሜት ለማሳደግ ያደረጋችሁት ቁርጠኝነት በሁላችንም ላይ የማይጠፋ አሻራ ጥሏል ለዚህም እናመሰግናችኋለን፡፡

መንግስት ያወጣውን የስፖርት ህግ አክብራችሁና ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ስርዓት ለአዲሱ አመራር አካላት ኃላፊነታችሁን በማስረከባችሁ እንዲሁም በቆይታችሁ ላደረጋችሁት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለኝን አክብሮት በሚኒስቴር መ/ቤቴ እና በራሴ ስም እገልጻጻለሁ ብለዋል፡፡

አያይዘውም የስፖርት ማህበራት፤ አመራሮች የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራር አካላት አርያን በመከተል በስፖርት ውስጥ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን፤ የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን በመፍታትና ለስፖርት ልማት ስራ የበኩላችሁን ድርሻ እንደምትወጡ ብለዋል።

በአዲስ ተመርጣችሁ የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት የተረከባችሁ አመራሮች አገራችን እንዲሁም ህዝባችን ከእናንተ ብዙ እንደሚጠብቁ አውቃችሁ በአትሌቲክስ ስፖርት ልማት ላይ ጠንክራችሁ በመስራት የአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም አደባባይ ላይ ያለውን የቀድሞ ዝናና ክብር እንደምትመልሱ እየተማመንኩ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለው በማለት የቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በመርኃ-ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር መኪዩ መሐመድ፦ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ምርጫ ዲሞክራሲያዊነት አድንቀው፤ በመንግሥት እና በስፖርት ማኅበራት መካከል ሊኖሩ ስለሚገቡ ግንኙነቶች፣ ስለፋይናንስ ሥርዓት እና የስፖርቱን ብሔራዊ ክብር ስለማስመለስና ስለመጠበቅ ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ለቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈጻሚዎች የምስጋና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን፤ ለረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ 30 ግራም ወርቅ፤ ለአትሌት ገዛኸኝ አበራ 20 ግራም ወርቅ ተበርክቶላቸዋል

Categories: Uncategorized