28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በመምረጥ ተጠናቋል ።
#############################################################
ታህሳስ 13/2017 ዓ.ም
በ28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለቀጣይ አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን የሚመሩት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመምረጥ ጉባኤውን አጠናቀዋል ።
በዚህም መሰረት :-
1.ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን -ፕሬዚዳንት
2.አትሌት መሠረት ደፋር
3.ወይዘሮ ሳራ ሀሰን
4.ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ
5.ዶክተር ኢፍረህ መሀመድ
6.አቶ አድማሱ ሳጂ
7.አቶ ቢኒያም ምሩፅ
8.ኢንጅነር ጌቱ ገረመው
9.ዶክተር ትዕዛዙ ሞሴ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት
በመሆን የተመረጡ ሲሆን ከሳምንታት በፊት በአትሌቶች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተመረጡት ኮነሬል አትሌት የማነ ፀጋይ እና አትሌት በላይነሽ ኦልጅራ በጉባኤው ተገኝተው ቃለ መኃላ ፈፅመዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ክብርት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በአመራርነት ቆይታቸው አብረዋቸው ለነበሩት አካላት በማመስገን አዲስ ለተመረጡት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ለአትሌቲክሱ እድገት ጠንክሮ መስራት እንዳለባቸው በመጠቆም መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ እና አደራ በመስጠት የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንቡን ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን
አስረክበዋል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በበኩላቸው ለተሰጣቸው እድል በማመስገን በአደረጃጀት ፣በሪፎርም በተለይም በስፖርት በማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ስራ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።ፕሬዝዳንቱ አክሎም ዘመናዊ የአትሌቲክስ ስልጠናን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳስበዋል ።
በጉባኤው ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ መኪዩ መሀመድ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያውያን ስፖርት ብቻ ሳይሆን ማንነት ጭምር ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክሎም አትሌቲክስ በአለም ያስተዋወቀን ገናና ስም እንዲኖረን ያደረገ የጥቁር ህዝቦች ኩራት መሆኑን በማንሳት ከዚህ ገናናነት ለምን ወደ ኋላ ተመለሰሰን ለምንስ የሜዳልያ ቁጥራችን ቀነሰ የሚለው ቁጭት አድሮባችሁ በትጋት እንድትሰሩ አሳስባለሁ ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ጀግኖች አትሌቶቻችን ትላንት የጻፋትን ታሪክ እያሰባችሁ ለማስቀጠል በርትታችሁ መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የተመረጡ አዲስ አመራሮች የተጣለባችውን ሀላፊነት በመወጣት ህዝብን በቅንነት እና በታማኝነት እንድታገለግሉ ሲሉ ከአደራም ጭምር ጋር አሳስበዋል።