20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር በዓድዋ ከተማ

በድምቀት ተከናውኗል ።

የካቲት 22/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በዓድዋ ከተማ በድምቀት ተካሂዷል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ፣ሸገር ከተማ በሁለተኝነት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ተጠናቋል ።

አትሌት ያለምዘርፍ የኃላው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ፤ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ከሸገር ከተማ ሁለተኛ፣ እንዲሁም አትሌት አሳየች አይቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፣ታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ጎልቶ በሚከበርበት የዓድዋ ከተማ ስኬታማ ውድድር አከናውነናል ካሉ ብኃላ ለዓድዋ ህዝብ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል ።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ የቡድን አትሌቶች የሜዳልያና የገንዘብ ሽልማት የተበረከት ሲሆን፤ በቡድን አሸናፊ ለሆኑ ክለቦች ደግሞ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እንደገና አበበ፣የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ዶክተር አፅብሃ ገብረእግዚአብሔር ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የዓድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋይ ገብረወልድ ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣የሚድያ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።

ለክልሎች ፣ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዕድል ለመፍጠር ፣ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና ክልሎች ፣ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች በማራቶን ሪሌ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ዓላማ ያደረገ ውድድር እንደሆነ ተጠቁመዋል።

በውድድሩ ላይ ክልሎች ፣ ከተማ አስተዳደር እና ክለቦች ተሳትፈዋል ።

በአለም አትሌቲክስ ደረጃ ኮርስ የወሰዱ 60 ዳኞች ውድድሩን መርተዋል።

Categories: Uncategorized