20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር በዓድዋ ከተማ በድምቀት ለማካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቀዋል ።

የካቲት 18/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በዓድዋ ከተማ በድምቀት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 20ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኮሙኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ምሩፅ እና የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በጋራ በመሆን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

ለክልሎች ፣ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዕድል ለመፍጠር ፣ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና ክልሎች ፣ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች በማራቶን ሪሌ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ዓላማ ያደረገ ውድድር መሆኑን በመግለጫው ተነስተዋል ።

በውድድሩ ላይ 3 ክልሎችና፣ አንድ ከተማ አስተዳደር ፣ 8 ክለቦች በድምሩ 12 ተቋማት፣ 36 ሴቶች 36 ወንድ በድምሩ 72 አትሌቶች ይሳተፋሉ ።

ውድድሩ የሚመሩ በአለም አትሌቲክስ ደረጃ ኮርስ የወሰዱ 60 ዳኞች መመደባቸው ፣ውድድሩን የሚመሩ የስራ ስምሪት መፈጠሩን እና ለውድድሩ በቂ በጀት መመደቡን በመግለጫው ተጠቁሟል ።

በቡድን ከ1ኛ-3ኛ ለሚወጡ የቡድን አትሌቶች የሜዳልያና የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም በቡድን አሸናፊ ለሚሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወይም ክለቦች የዋንጫ ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።

Categories: Uncategorized