የዓለም አትሌቲክስ አንደኛ ደረጃ አሰልጣኝነት እና ዳኝነት ስልጠና “የምርቃት መርሀግብር ” ተከናወነ ።
##################################################
ጥር 19/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አትሌቲክስ አንደኛ ደረጃ ስልጠና የምርቃት መርሀግብር አከናወነ ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበጀት ዓመቱ በእቅድ ይዞ ከሚያከናውናቸው በርካታ የልማት ተግባራት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ስልጠና ነው።
በምርቃት መርሀግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ለተመረቁ ሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ስልጠና ላይ በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን በመጠቆም የዓለም አትሌቲክስ 1ኛ ደረጃ አሰልጣኝነትና ዳኝነት ስልጠና ዓላማው የሀገር ውስጥ 2ኛ ደረጃ ስልጠና ወስደው የላቀ ውጤት ያላቸውን አሰልጣኝና ዳኞችን የአለም አቀፍ ስልጠና በመስጠት በዘርፉ ያሉትን የአሰልጣኝነት እና ዳኝነት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሆነ አንስተዋል ።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ስልጠናው በኢትዮጵያውያን ኢንስትራክተሮች መሰጠቱን አድንቀው ፣እንደ ሀገር የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ኢንስትራክተሮች አናሳ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑንና በቀጣይ የአሰልጣኞች ቁጥር ለማሳደግ በትኩረት የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነትና በመጠቀም የሁለተኛ ደረጃ ስልጠና እንዲሰጥ አበክረው እንደሚሰሩ ገልጿል ።
ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻም ለተመራቂዎች በሚሄዱበት የስራ መስክ ሁሉ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማቸው በመመኘት በስልጠናው ያገኙትን እውቀት እንዲተገብሩ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመርሀግብሩ ላይ ለተመራቂዎች የሰርተፊኬት ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ፣አሰልጣኝ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተሮች እና ተመራቂ ተወካዮች ስለ ነበረው ስልጠና ቆይታቸው ንግግር አድርጓል ።
የአሰልጠኝነት ስልጠና ከጥር 07/2017 -18/2017 ዓ.ም የተሰጠ ሲሆን የዳንኝነት ስልጠና ከጥር 14-18 /2017 ዓ.ም በአዲስአበባ ስፖርት ስልጠና ማዕከል ተሰጥቷል ።
አሰልጣኝነት ስልጠናው ላይ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች እና ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ እንዲሁም ዳኝነት ላይ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ ሰልጣኞች ተሳትፈዋል።
የዓለም አትሌቲክስ አንደኛ ደረጃ አሰልጣኝነት እና ዳኝነት ስልጠና ላይ በአሰልጣኝነት 24 እና በዳኝነት 20 ተሳታፊ ስልጠና ወስደዋል።




