የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌቶች ጋር ስኬታማ ውይይት አደረገ ።
የካቲት 19/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከአትሌቶች ጋር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስኬታማ ውይይት አድርጓል ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ከአትሌቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ እና ቀጣይነት ያለው ተግባራት ለመስራት መዘጋጀታቸውን በማንሳትና በእቅድ ውስጥ በማካተት ከአትሌቶች ጋር በርካታ ስራ ለመስራት በቁርጠኝነት እንደሚተገበር በመጠቆም ውይይቱን አስጀምረዋል ።
የፌዴሬሽኑ ውድድር እና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች እና አሰልጣኞች መምረጫ መመሪያ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የመመሪያው ዓላማ አገር ወክለው የሚሰለፋ አትሌቶች ግልጽ ፣ፍትሀዊና ተጠያቂነት ባለው ስርዓት በመምረጥ ውጤታማ አትሌቶችና አሠልጣኞች ለማፍራት እንደሆነ አንስተዋል ።
ወይዘሮ ቅድስት ታደሰ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የህክምና ባለሞያ የፀረ አበረታች ቅመሞች፣የመገኛ አድራሻ ፣ሴፍ ጋርዲንግ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቪዛ ጉዳይ፣የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረትና ፣የትራክ ችግር እና የአትሌቶች መምረጫ መስፈርት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አትሌቶቹ በስፋት ጠይቀዋል ።
በመድረኩ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ከአትሌቶች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ፣የማዘውተሪያ ስፍራና የትራክ ጉዳይ እንደ አገር አሳሳቢ መሆኑን በማንሳት ከመንግሥት በተለይም ደግሞ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ውጤታማ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።
ፕሬዝዳንቱ አክሎም የቪዛ ጉዳይ ለመፍታት ከአውሮፓ ህብረት እና ከተለያዩ ኢምባሲዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንና ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ተስፋ ሰጪና አበረታች ምላሽ መገኘቱን በመናገር ችግሩ ለመፍታት አሁንም ቀጣይነት ጥረት እንደሚያደርጉ አሳስቧል ።
በመድረኩ ላይ የኢ.አ.ፌ. ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፣የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌቱ ገረመው፣የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር ጨምሮ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን ከአትሌቶች ጋር ሰፊና ስኬታማ ውይይት በማድረግ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ እና ምላሽ የተሰጠ ሲሆን የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ውይይቱ ተጠናቀዋል ።




