የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የአትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አበረታች ቅመሞች ወንጀሎችን ለመከላከልና የናሙና ምርመራ ላብራቶሪ ለማቋቋም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የካቲት 19/2018 ዓ.ም
የኢትዮዽያ ፌደራል ፖሊስ ኮምሽንን ወክለው ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ወክለው ክብርት ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የመግባቢያ ስምምነቱን ፈርመዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የመግባቢያ ሥምምነቱ ጤናማና ንፁህ ስፖርትን ለማበረታታት እንዲሁም የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ ፍይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የመግባቢያ ሥምምነቱ አትሌቶችን ከወንጀል በመጠበቅ የሀገራችንን ስፖርት በተሻለ መንገድ ለማሳደግ የሁለትዮሽ ስምምነቱ የላቀ ሚና እንዳለው አክለዋል።
ክብርት ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የውል ሥምምነቱን አስመልክቶ እንደገለፁት መንግስት የስፖርት ልማትን ከማዘመን ባሻገር የስፖርተኞችን ጤንነት ለመጠበቅ በቴክኖሎጅ የበለፀጉ ተቋማትን እያቋቋመ ነው ብለዋል።
የአበረታች ቅመም ወንጀሎችን ለመከላከል የናሙና ምርመራ ላብራቶሪ በሀገራችን መቋቋሙ ለሀገሪቱ ስፖርት ልማት ትልቅ ስኬት እንዳለውም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ሥምና ክብር ለማሳደግ ጤናማ ስፖርተኞችን መፍጠር ቀዳሚ ስራ እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሸን ጋር የተደረገው የውል ስምምነት በቅንጅት ለመስራት ፋይዳው የላቀ መሆኑም አክለዋል
ክቡር መኪዩ መሐመድ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመግባቢያ ሥምምነቱ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ክቡር መኪዩ የመግባቢያ ስምምነቱ የስፖርተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት፣ አህጉር አቀፍ መሪነትን ለማጠናከር፣ የሥራ እድል ለመፍጠር እንዲሁም ጤናማ የስፖርት ከባቢን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የምርመራ ላብራቶሪው መቋቋም ወጪን ለመቀነስ፣ የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ የምርመራ ሂደትን ለማፋጠንም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግሯል።
ዓለም አቀፍ ተቋም በሀገራችን መቋቋሙ ለሀገር ክብር ጭምር እንደሆነ የገለፀው ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን በጋራ ለመስራት ሥምምነቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በመግባቢያ ሥምምነቱ ላይ የተገኘው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ የሀገራችን ስፖርተኞች የምርመራ ሂደት ለማሻሻል፣ በአቋራጭ ውጤት ለማምጣት ህገወጥ ስራ ለሚሰሩ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል ብሏል።
የውል ሥምምነቱ ንፁህ ስፖርት እንዲስፋፋ፣ ፍትሐዊ የውድድር መድረክ ለመፍጠር፣ የአለም አቀፍ ፀረ አበረታች ቅመሞች ህግን ለማክበር እንዲሁም የስፖርት ነክ ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው።
በመግባቢያ ሥምምነቱ ላይ ክብርት ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ ክቡር መኪዩ መሐመድ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።






