የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አብሮ ለመስራት የጋራ መግባቢያ ስምምነት አደረጉ
========================================
የካቲት 13/2018 ዓ.ም (ኢሚ) በኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫን ዓለማቀፋዊ ይዘት ኖሮት እንዲከናወን የሚያስችል የጋር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ወክለው የፈረሙት የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ አስተባባሪ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አትሌት ስልሽ ስህን የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙ ሲሆን የስምምነቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫን ዓለማቀፋዊ ስዳንዳርዱን ያሟላ በማድረግ ለአትሌቶች የስኬት አንዱ መንገድ እንዲሆን ለማስቻልና የሌሎች ዓለም ሀገራት ታዋቂና አዳዲሲ አትሎቶችን ያካተተ ሆኖ እንዲቀጥል ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት አትሌት ስለሽ ስህን እንደገለፁት ስምምነቱ የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ ዓለማቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ ሆኖ እንዲከናወን በማድረግ የሀገራችን የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚተዋወቁበት ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው የሩጫ ሂደቱን የተሻለና ውጤታማ በማድረግ ረገድ አዳዲስና የወደፊት ፈንጠዝያዎች(surprise) እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ አስተባባሪ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በበኩላቸው በኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የተከናወነው የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫን ዓለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ በሩጫው የተሻለ ሰዓት የሚያስመዘግቡ አትሌቶች የሚያስመዘግቡት የሰዓት ሪከርድ ዓለማቀፍ ስታንዳርዱን ያሟላ ሆኖ እንዲመዘገብ በማስቻል አትሌቶች በሌሎች ዓለማት በሚከናወኑ የሩጫ ውድድሮች እንዲወዳደሩ የሚያስችል በመሆኑ ለክለቦችና አዳዲስ አትሌቶች አዲስ እድል የሚፈጠር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ አብዱልፈታ አክለውም 4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 18/2018 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ተጀምሮ መስቀል አደባባይ የሚጠናቀቅ መሆኑን በመጥቀስ ሩጫው የሀገራችንን ምርት በማስተዋወቅ፣ የዘርፉን ተዋናዮች የእርስበርስ ትውውቅና የስራ ግንኙነት በማሻሻል እና የአምራች ኢንዱስትሪ ሰራተኛው ጤንነቱን እንዲጠብቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡








