(ኢ. አ.ፌ) ታህሳስ 26/2018ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲያካሄድ የቆየው የክለቦች የአጭር፥ የመካከለኛ፣ የ3000 ሜ መሠናክል ፣የሜዳ ተግባራትና የርምጃ ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።
ክብርት ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፣ ክቡር መኪዩ መሐመድ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፣ ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት እና አንጋፋ አትሌቶች በተገኙበት መርሃ ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።
ክብርት ሸዊት ሻንካ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት አትሌቲክስ የሀገራችን መለያ የሆነ ስፖርት በመሆኑ አትሌቲክሱን ለማዘመን መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል።
መንግስት የአትሌቲክስ ስፖርትን ወደ ነበረበት ክብርና ዝና ለመመለስ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት፣ በአህጉርና አለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች ጭምር ድጋፍ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቅርብ ጊዜ ወድህ በአዲስ ሪፎርም እየሰራቸው ያሉ ስራዎች የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ የገለፁት ሚኒስትሯ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን በማጠናከር ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ዶ/ ር አመንሲሳ ከበደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የውድድር ተሳትፎ አቅምን ከፍ ለማድረግ፣የአገር አቀፍና አለም አቀፍ ውድድሮችን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ ፣የሀገር ውስጥ ውድድሮች ከፍ ባለ ደረጃ እንዲካሄዱ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር እየሰራ መሆኑን ነው የገለፁት ዶ/ር አመንሲሳ ከበደ።
የፋሲሊቲ እና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ በአዲስ ሪፎርም እንዲደራጅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጎን ሆኖ እያገዘ እንደሆነም ገልፀዋል።
አለም አቀፍ ስታንዳርድን ባሟላ ትራክ ላይ ውድድሮች እንዲካሄዱ የፈቀደው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ከፍ ባለ ደረጃ በማካሄድ አለም አቀፍ ደረጃን እንዲመጥን ለማድረገ እንደሆነ ነው ዶ/ር አመንሲሳ የገለፁት።
ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድርን እንዲታዘጋጅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፌዴሬሽኑ እየደገፈ እንደሚገኝም አክለዋል።
በመጨረሻም ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና ሰርተፊኬት በመስጠት መርሀግብሩ ተጠናቀዋል።

















