ኢ.አ.ፌ ጥር 1/2018ዓ.ም አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና በጃፓን የስፖርት ልዑካን መካከል በተካሄደው የሁለትዮሽ ግንኙነት ውይይት የአትሌቲክስ ዘርፉን ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌቱ ገረመው፣የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሰረት ደፋር፣የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ፣ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣እና የጽ/ቤቱ ሀላፊ ዶክተር አመንሲሳ ከበደ ከልዑኩ ጋር ሰፊ እና ውጤታማ ውይይት አድርጓል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የጃፓን የስፖርት ልዑካን ባደረጉት ውይይት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተነስቷል።

በዚሁ መሰረት ሁለቱ ሀገራት በአትሌቲክስ ስፖርት ዙሪያ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ፣ የስልጠና ማዕከላትን በማዘመን ፣ በቴክኖሎጅ የታገዙ ስልጠናዎችን በመስጠት የውድድር አይነቶችን በማስፋፋት ላይ አብሮ ለመስራት ያለመ ስኬታማ ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በአለምአቀፍ አትሌቲክስ ውስጥ ያላትን የመሪነት ሚና ለማጠናከር በጃፓን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ በውይይቱ ከተነሱ ነጥቦች መካከል ተጠቃሽ ነው።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያላትን የላቀ ልምድና ተሞክሮ ለጃፓን ሀገር እንድታካፍል ልዑካኑ በውይይቱ ጠይቋል ።

ለአለም አትሌቲክስ ሞደል የሆኑ አንጋፋ አትሌቶች በጃፓን ትምህርት ቤቶች ላይ ስለ አትሌቲክስ ባህል፣ ፅናት እና ውጤታማነት ዙሪያ ልምድና ተምክሮዎች እንዲያጋሩ የጃፓኑ ልዑካን በውይይቱ አንስቷል ።

በሌላ መልኩ ጃፓን ስፖርትን ለኢኮኖሚ፣ ለድፕሎማሲ እና ለቱሪዝም ከመጠቀም አንፃር ያላትን የተሻለ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል አብሮ መስራት ላይ ተወያይተዋል።

በአለም አቀፍ ግንኙነቶች ፣ በስፖርት ግብአት፣ በባለሙያዎች አቅም ግንባታ ፣ የስልጠና አሰጣጥ ደረጃዎችን በማሻሻል ድጋፍ በማድረግ አብሮ ለመስራት በጃፓን በኩል ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ በውይይቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እና ጃፓን የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ ስትራቴጅካዊ አጋርነት ያለው የሁለትዮሽ ስምምነት በቀጣይ እንደሚደረግ በውይይቱ ተካቷል።

Categories: Uncategorized