Maichew athletes'

ታህሳስ 27/2010 ዓ. ም. ዜና አትሌቲክስ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የቴክኒክ ዳይሬክተሩ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቆጂ ከተማ የሚገኘውን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልን እና በአሰላ ከተማ የሚገኘውን በወ/ስ/ሚ/ር የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባን የስፖርት አካዳሚ ታህሳስ 26/2010 ዓ. ም. ጎብኝተዋል፡፡

አመራሮቹ በስፍራዎቹ በመገኘት ከማዕከሉና ከአካዳሚው አመራሮችና ከአትሌቶቹ ጋር በአትሌቲክሱ ዙሪያ ሰፊ ምክክር ከማድረጋቸውም በላይ የአትሌትነት ህይወት ተሞክሯቸውን ለሰልጣኞቹ አካፍለዋል፡፡ በምክክሩ ወቅት ከተነሱ በርካታ ጉዳዮች መካከልም የስልጠና ስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ማነስ፣ የስልጠና ቁሳቁሶችና የጂም አለመሟላት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

በተነሱት ጉዳዮች ላይ ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በሰጠው ምላሽ ፌዴሬሽኑ ዋነኛ ትኩረቱ የሃገሪቱን የአትሌቲክስ ውጤት፣ ዝናና ክብር ወደቀድሞው ከፍታው ለመመለስ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ለሰልጣኝ አትሌቶች አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ወደኋላ የማይልና የማያመነታ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አያይዞም ከስልጠና ቁሳቁሶች አቅርቦት ጋር በተገናኘ ፌዴሬሽኑ ከክልሎቹ ጋር ሆኖ ሊያሟላ የሚችላቸው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን የማሟላቱ ስራ እንደተጠበቁ ሆኖ ነገርግን እንደሌሎቹ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች እንደሚገኙት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ሁሉ የበቆጂ ማዕከልም በአካባቢያችሁ በሚገኙ ቁሳቁሶች የመለማመጃ መሣሪያዎቹን እዚሁ በሃገር ውስጥ በመስራት መጠቀም እንደሚቻልና በተለይ በአማራና በትግራይ ክልሎች የሚገኙት ሁለቱ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በራሳቸው ተነሳሽነት በአካባቢያቸው በሚገኙ ቁሳቁሶች ከውጪ ሃገራት በከፍተኛ ወጪ ሊገዙ የሚችሉትን ውድ የስልጠና ቁሳቁሶች በማሟላት ግንባር ቀደም አርአያ መሆን በመቻላቸው የነዚህን ክልሎች ተሞክሮ ወደ በቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ በማምጣት ጊዜያዊና አፋጣኝ መፍትሄ አድርጎ መጠቀም እንደሚቻል በምክክሩ ወቅት አስረድቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜና ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጣኝ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና አመራሮች ታህሳስ 22/2010 ዓ. ም. ማዕከሉ የሚገኝበት ስፍራ በመገኘት ሙሉ የአትሌቲክስ ስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድጋፉ ወቅት ሰልጣኞቹና የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ሙልዬ አብርሃ በፌዴሬሽኑ ለተደረገላቸው የአትሌቲክስ ስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Similar Posts
Latest Posts from