ለ22ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒና ልኡካን ቡድናችን ደማቅ አቀባበልና የገንዘብ ማበረታቻ ተሰጠው፤
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ22ኛ ጊዜ በሞሪሽየስ በተካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተካፍሎ በ4 ወርቅ፣ በ6 ብር፣ በ4 ነሃስ፣ በድምሩ በ14 ሜዳልያ ከተሳታፊ የአፍሪካ ሃገራት 5ኛ ደረጃን በመያዝ በድል ወደ ሃገሩ ኢትዮጵያ ለተመለሰው የልኡካን ቡድናችን ደማቅ አቀባበል አካሂዷል፡፡
ዛሬ ረቡእ ሰኔ 8/2014 ዓም. ከማለዳው 3፡30 ላይ በአራራት ሆቴል በተካሄደ የአቀባበልና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚ/ር የስፖርት ዘርፍ ሚ/ር ዴኤታው ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ አቶ አምበሳው እንየው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ፍቃዱ መኩሪያ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአስተዳደር ልማት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር.፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚና ማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት፤ የመከላከያ፣ የኢት/ን/ባንክ፣ የፌዴ/ማረሚያና የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለቦች አመራሮችና የቦርድ ኃላፊዎች በአቀባበሉ መርኃ ግብር ላይ የተገኙ ሲሆን ለልኡካን ቡድኑ አባላት በኢአፌ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር በዛብህ ወልዴ አማካኝነት ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት የአበባ ጉንጉን አበረክተዋል፡፡
አጠቃላይ የቡድኑን የሞሪሽየስ ቆይታ በተመከተም የቡድን መሪዋና የኢአፌ ሥራ አስፈፃሚ ኮ/አባል ወ/ሮ ፎዚያ ኢድሪስ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን መርተው ይዘውት በሄዱት ቡድን ውጤት ታላቅ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው፣ ነገር ግን የቡድኑ ውጤት ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ይችል እንደነበረ ጠቅሰው ኮቪድ መልኩን እየቀያየረ መሰናክል ሆኖ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ክብርት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ካውንስል አባል፣ የምስ/አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን ም/ፕሬዝዳንትና የኢአፌ ፕሬዝዳንት በበኩሏ ውጤቱ በአትሌቲክሱ ቤተሰብ ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን ከመፍጠሩም በላይ ለቀጣይ ውድድሮች ያሉንን ጥንካሬዎች በማስቀጠልና ድክመቶቻችንን አስተውለን ለማረም እድል የሰጠ እንደነበር፤ በዝግጅት ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ መከላከያና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ ስፖርት ክለቦች በጂምናዝየምና በሜዳ ፍቃድ ከፌዴሬሽናችን ጋር ሲተባበሩ የቆዩ በመሆናቸው ምስጋና አቅርባ በወርቅም ሆነ በሌሎች ሜዳልያዎች ብዛት የአሁኑ ውጤት ከቀደሙት ትልልቅ ድሎቻችን ተርታ የሚመደብ በመሆኑ በቡድኑ ኩራት እንደተሰማት ጠቁማለች፡፡
በመጨረሻም የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁና እንኳን በድል ተለመሳችሁ መልእክት መንግስት በውጤቱ በጣም ደስተኛ መሆኑና ሁልጊዜም ከአትሌቲክሱ ጎን ሆኖ እንደሚደግፍ፣ ለአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ ከወዲሁ ሁሉም ዝግጅት መጀመር እንደሚገባውና በመንግስት በኩል መደረግ የሚገባውን ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግ ጠቁዋል፡፡
በዛሬው እለት ለአጠቃላይ ለልኡካን ቡድኑ አባላት በተከናወነው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አሰጣጥ መሰረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብር 1,148,500.00 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቲ አርባ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር) ገደማ ለሽልማት ወጪ አድርጓል፡፡
 
ኢትዮጵያ ሁሌም ታሸንፋለች!
 
Similar Posts
Latest Posts from