39ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል እና 1ኛው የምሥራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፤
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመታዊ የውድድር ካላንደር መሰረት የካቲት 6/2014 ዓ.ም ለ39ኛ ጊዜ በጃን ሜዳ የሚካሄደውን የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል እና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውና ኢትዮጵያ እንድታካሂደ እድሉን ያገኘችበት በምሥራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር ዙሪያ ጉርድሾላ በሚገኘው የፌዴሬሽኑ መሰብሰቢ አዳራሽ ቁጥራቸው በርካታ ለሆኑ የስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎች ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የፌዴሬሽኑ ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የፌዴሬሽኑ አቃቤ ንዋይና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር በዛብህ ወልዴ፣ የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፣ የተሳትፎና ውድድር ንኡስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ፣ የህክምና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን እና የተሳትፎና ውድድር ባለሙያው አትሌት አሸብር ደምሴ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በየተራ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የውድድሩ አላማ ለተተኪ አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር ቀዳሚው ሲሆን፣ አትሌቶች የስልጠና ዝግጅታቸውን በውድድር እንዲፈትሹ ማስቻል ሌላኛው መሆኑንና ክለቦች፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ሁሉም የውድድሩ ተካፋዮች ያሉበትን የአገር አቋራጭ ስልጠና አቋም በውድድር የሚፈትሹበት እንደሆነ ተገልጧል፡፡
በዘንድሮው 39ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ለየት የሚለው ጉዳይ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የአገር አቋራጭ ውድድርን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧ ሲሆን አገራችንም ውድድር የማዘጋጀትና የማስተናገድ አቅሟ የሚፈተሸበት መሆኑ እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የአፍሪካ አገራት ከሚገኙበት የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን አባል አገራት ሁሉም የተጋበዙ ቢሆንም ከ10ሩ መካከል አምስት ሃገራት እስከ አሁን በውድድሩ ለመሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተጠቁሟል፡፡
ውድድሩ እሁድ የካቲት 6/2014 ከማለዳው 1፡00 ጀምሮ እስከ 6፡00 ድረስ በጃን ሜዳ የሚካሄድ ሲሆን በአካል ጃንሜዳ ተገኝተው መከታተል ለማይችሉ የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች በዋልታ ቴሌቪዥን ሙሉ ዝግጅቱ በቀጥታ ከጃንሜዳ የሚተላለፍ እንደሆነም ተወስቷል፡፡
ለዚህ ውድድር ማካሄጃ ፌዴሬሽኑ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን፣ ከ840 ሺህ ብር በላይ ለአሸናፊዎች ሽልማት መዘጋጀቱን፣ ከ180 በላይ የአትሌቲክሱ ባለሙያዎች በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የሚሳተፉ መሆናቸው፣ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ፈቃድና እውቅና የተሰጣቸው የአትሌቲክስ ዳኞች ውድድሩን እንደሚመሩትም ከመግለጫው ማብራሪያ ታውቋል፡፡
ዝርዝር ጉዳዮች ከሥር በተያያዙት መረጃዎች ላይ ይገኛሉ፡፡
 
Similar Posts
Latest Posts from