ህዳር 17/2010 ዓ. ም. አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ አስቸኳይ ስብሰባ በክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን በመወያያ አጀንዳዎቹ ቅደም ተከተል መሰረት ፌዴሬሽኑ በ21ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ወቅት በመተዳደሪያ ውስጠ ደንቡ ላይ ተወያይቶ በቀጣይ ስብሰባ በጥልቀት ታይተው ውሳኔ ሊያገኙ ይገባቸዋል ባላቸው አንቀጾች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ በቀረቡ ማሻሻያዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰ ሲሆን በተለይ በክለቦች የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ውክልና ዙሪያ በጥልቀት ውይይት አካሂዷል፡፡
ከጉባኤው መጀመር አስቀድሞ በ17ኛው የቶታል ኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዝባዊ ሩጫ ወቅት በ2 ኢትዮጵያውን ላይ ባጋጠመው ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት ጉባኤው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን የገለጸ ሲሆን የ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎትም አድርጓል፡፡

በመቀጠልም በአጀንዳው መሰረት ቢያንስ 5 ክለቦች ያሉት የክልል/ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2 አትሌቶች ተወክሎ በፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ በድምጽ እንዲሳተፉ የቀረበው ሃሳብ በ20 የድጋፍና በ3 የተቃውሞ ድምጽ ሃሳቡ አልፏል፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን ሊያሰሩ የማይችሉ ሃሳቦችና አካሄዶች ካሉ በቀጣዩ ጉባኤ ቤቱ ተወያይቶባቸው ሁሉንም አባል ፌዴሬሽኖች ሊያግባባ በሚችል መልክ ሊቃኙ እንደሚችሉ በጉባኤው የጋራ አቋም ተወስዷል፡፡

በአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አሰራር መሰረት በፌዴሬሽኖች ውስጥ ያለውን የአመራር ሰጪነት ሚና ሴቶችም ሊቀላቀሉት እንደሚገባ በደነገገው መሰረት ፌዴሬሽኑ 30 በመቶ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን የሴቶች ተሳትፎ ማሳደግ ችሏል፡፡ ይህም ለሌሎች ማህበራት፣ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ጅማሬ አከናውኗል፡፡ የምርጫ ስርዓትን በተከተለ መንገድ ምርጫውን በአስመራጭ ኮሚቴ ስያሜ ያካሄደው ፌዴሬሽኑ ፍጹም ግልፅና አሳታፊ በሆነ ሂደት አስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ሂደቱን መርቷል፡፡

በዚህም ከቀረቡ 17 ሴት እጩ ተፎካካሪዎች መካከል ጀግናዋ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከኦሮሚያ ክልል በከፍተኛ ድምጽ 1ኛ ሆነው ያለፉ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን እንዲሰሩም ተመርጠዋል፡፡
ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በተካሄደው ምርጫ 2 ተፎካካሪዎች (ወ/ሮ አዚዛ አብዲ ከኦሮሚያና ወ/ሮ ፎዚያ ኢድሪስ ከአፋር ክልል) እኩል ድምፅ በማግኘታቸው ድጋሚ የመለያ ምርጫ ተካሂዶ ወ/ሮ ፎዚያ ኢድሪስ ከአፋር ክልል በከፍተኛ ድምጽ በመመረጣቸው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የስብሰባ የመጨረሻ አጀንዳ የነበረው የ2009 በጀት አመት የሱፐርቪዥን ሪፖርትና ቀጣይ ተግባራት በተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎ የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ዳይሬክተር የቀረበ ሲሆን አመታዊ የሃገር ውስጥ ውድድሮች መርሃ ግብር ላይም መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በተጓዳኝ ፌዴሬሽኑ የሰንዳፋ በኬ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ መንደር ግንባታን ከምንግዜው በላቀ ሁኔታ አጠናክሮ ለመቀጠል እየሰራ እንደሚገኝ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ የገለጸ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ከዋናው ቢሮ ጎን የራሱ የሆነ ጂምናዝየምና ሌሎች መሟላት የሚገባቸውን የስፖርት ፋሲሊቲዎች ለማደራጀት ከመሬት መረከብ ጀምሮ ተጨማሪ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ጨምሮ ለጌባኤው አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም አስቸኳይ ስብሰባው በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት በክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ መዝጊያ ንግግር ተጠናቋል፡፡

Similar Posts
Latest Posts from