የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ የቶኪዮ 2020 (2021) ኦሊምፒክ አትሌቲክስ ቡድንን በልምምድ ስፍራ ተገኝተው ስልጠናውን በመመልከት አትሌቶችን አበረታቱ፤
 
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቶኪዮ 2020 (2021) ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ቡድኑን መልምሎ ከህዳር/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሆቴል በማስገባት ላለፉት 8 ወራት ጠንካራ ልምምድ እንዲያገኝ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ለረጅም ወራት ሆቴል በመቀመጥ ሲካሄድ የቆየውን በኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ዝግጅትና የስልጠና ሂደት ክብርት ወ/ሮ ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት በዛሬው እለት ረብዑ ሰኔ 30/2013 ዓ. ም. ከማለዳው 3፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመገኘት ተከታትለዋል፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀ/ም/ፕሬዝደንት፣ የኢአፌ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ የተገኙ ሲሆን ክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ ለልኡካን ቡድኑ ባስተላለፉት መልእክት የቀደሙ የሃገራችን የአትሌቲክስ ጀግኖች ቁጥራቸው የትየለሌ ሲሆን የነዚህን ጀግኖች የሃገር ወዳድነት መንፈስ በመከተል የዛሬዎቹ አትሌቶች ተረድተውና ተጎናፅፈው ለኢትዮጵያ እንዲጠቅም ወደ ውጤታማነት በመቀየር አ.ኤ.አ በ1964 በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በድል ያስጠራትን የጀግናውን ሻምበል አበበ ቢቂላ ታሪክ እዚያው ቶኪዮ፣ ጃፓን ላይ በብዙ የውድድር ዲሲፕሊኖችም በመድገም ኢትዮጵያ ዛሬም ታሪክ ሰሪ ትውልድ ያላት ምድረ-ቀደምት ገናና ሃገር መሆኗን ለአለም ህዝብ ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡
አያይዘውም እኛ ከአትሌቶቻችን የምንጠብቀው በአትሌቲክሱ ድላቸውን ስለሆነ አትሌቶች ሙያቸው ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡
የአትሌቲክስ ቡድኑን በመወከል አትሌት የኋልዬ በለጠው እና አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሆቴል ገብተው የተከታተሉት ስልጠና ምን ይመስል እንደነበር የገለጹ ሲሆን መንግስት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት አትሌቲክሱ ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንደምትሆን ተናግረዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦም የቡድኑን አሰልጣኞች ወክለው በሰጡት አስተያየት ቆይታቸው ከእስከዛሬ ኦሊምፒኮች የተለየና በጣም ጥሩ እንደነበረ፣ በተሳተፉባቸው በርካታ ኦሊምፒኮች በሃገር ደረጃ በልምምድ ስፍራ ተገኝቶ የጎበኛቸውና ያበረታታቸው የሃገር መሪ እንዳልነበረና ክብርት ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ በመሆናቸው ክብርት የኢፌዲሪ ፕሬዝደንትን አመስግነዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘንድሮው ኦሊምፒክ በሁለቱም ፆታ በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል፣ በማራቶንንና በሴቶች የእርምጃ ውድድር በአጠቃላይ 34 አትሌቶችን ይዛ ጠንካራ ተፎካካሪ ሃገር ትሆናለች፡፡
ድል ለአትሌቶቻችን!
 
Similar Posts
Latest Posts from