የቶኪዮ 2020 (2021) ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ስልጠናና ዝግጅት፣
***********************************************
ካለፉት 7 ወራት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ ለቆየው የቶኪዮ 2020 (2021) ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ዝግጅት ግልጽ የሆነ የመምረጫ መስፈርት በማዘጋጀት ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መንገድ አትሌቶችንና አሰልጣኞችን ከመመልመል ጀምሮ አትሌቶች በመረጡት ሆቴል ገብተው ሁለንተናዊ የስልጠና ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ፌዴሬሽኑ የሃገር ውስጥና አለም አቀፍ የማጣሪያ ውድድሮችን በማድረግም ከአጭር ርቀት ጀምሮ እስከ ማራቶን፣ የ3000 ሜትር መሰናክልንና እርምጃን ጨምሮ በሁለቱም ፆታ አገራችንን ኢትዮጵያን ሊወክሉና ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉትን የመጨረሻ ተሰላፊዎችን ከነተጠባባቂዎች ለይቷል፡፡
ከልየታ ሥራው ባሻገርም ስልጠናው ያልተቋረጠ፣ ዘመናዊ እና ሳይንሳዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግም በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል፡፡
ቡድኑ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 23/2013ዓ.ም. ከማለዳው 1፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ግቢ ውስጥ በሚገኘው ዘመናዊ የማዘውተሪያ ስፍራ ላይም የመካከለኛ፣ የረጅም ርቀት፣ የመሰናክልና ማራቶን ቡድን ጠንካራ ልምምድ ሲሰራ አርፍዷል፡፡
በዚህ የልምምድ እለት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራን ጨምሮ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ አቶ ቢኒያም ምሩፅ የአዲስ አበባ ከተ/አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የሚመለከታቸው የኢ.አ.ፌ. ባለሙያዎች በስፍራው በአካል በመገኘት የስልጠና ሂደቱን የተከታተሉ ሲሆን የአንድነት መንፈስ እንዲጎለብት፣ በመተባበር ድል ማድረግ እንደሚቻል በመግለፅ የቡድኑን አባላት በምክር አበረታትተዋል፡፡
ድል ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ቡድናችን!!
 
Similar Posts
Latest Posts from