የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ ከሱማሌ ብ/ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ጋር በአትሌቲክስ ልማትና ውጤታማነት ዙሪያ ተወያዩ:-
ትላንት የካቲት19/2013 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ በመገኘት የፌዴሬሽናችን ፕሬዝዳንት ክብርት ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ ከክቡር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ጋር አትሌቲክስን በምስራቁ የሀገራችን ክፍል በተለይም በሱማሌ ክልል በስፖርቱ ከተሳታፊነት ባለፈ ወደ ውጤታማነት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በክልሉ ከፕሮጀክት ውጭ የስልጠና ማዕከልም ሆነ ክለቦች ባለመኖራቸው አትሌቶች ከፕሮጀክት ወደ ስልጠና ማዕከል በመቀጠልም ወደ ክለቦች ገብተው ተከታታይነትና ወጥነት ያለውና ቅብብሎሹን የጠበቀ ስልጠና እንዳያገኙ ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆኑ በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት ክለብ እንዲያቋቁሙ እንዲሁም የክልሉ መንግስት የማሰልጠኛ ማዕከል እንዲኖር ከፍተኛ ስራ መስራት እንደሚገባ በውይይቱ የተነሳ ጉዳይ ነው፣ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች እንደ ችግር የሚነሳውን የአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ለመቅረፍ በስፋት መስራት የሚስችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች አጠናክሮ መስራት እንደሚገባ በውይይታቸው ተነስቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የክልሉ ስፖርት ቢሮና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ቅደም ተከተል አውጥተው በሚያቀርቡት መሰረት ስፖርቱን ለማሳደግ የክልሉ መንግስት እንደሚሰራ ክቡር አቶ ሙስጠፌ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ኮ/ር ደራርቱ ቱሉ በውይይቱ እንዳነሱት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየክልሉ የሚገኙ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች የቢሮ አደረጃጀቶችና አሰራሮች ጠንካራ እንዲሆኑና በፋይናስ ራሳቸውን ችለው ዘላቂ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ባለው ፅኑ አቋም በሱማሌ ክልል የሚገኘውን አደረጃጀት የተሻለና ውጤታማ ለማድረግ በሙያና በቴክኒክ ለማገዝ ከክልሉ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ክቡር አቶ ኢብራሂም ኡስማን የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት፣ ክቡር አቶ ኡመር ሰይድ የክልሉ የስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ ዶ/ር ሀሰን ቃሲም የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወ/ሮ ማስተዋል ዋለልኝ የፌዴሬሽኑ የሰው ኃብ/ንብ/አስተዳደር መሪ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና የጽ/ቤት ኃላፊ ባለፈው ሳምንት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል በሱማሌ ብ/ክልል፣ በሀረሪ ብ/ክልል እና በድሬደዋ ከተ/አስተዳደር በመገኘት በየክልሎቹና ከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
Similar Posts
Latest Posts from