ይህ እለት እሁድ ህዳር 13/2013 ዓ.ም. በሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ2016 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሐምሌ 29 እስከ ነሃሴ15/2008 ዓ.ም. በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ ለ31ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 18 ወንድ እና 17 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል፣ በእርምጃ እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የሪዮን አየር ንብረት መሰረት ባደረገ ሁኔታ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እንዲሁም በደብረዘይት፣ በሶደሬ፣ አዋሽ፣ አዋሳ መስመር እና ወለንጪቲ ባሉ ከተሞች በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ኮ/ር ሁሴን ሼቦ፣ ንጉሴ ጌቻሞ፣ ብዙአየሁ ታረቀኝ፣ ሻለቃ ባዬ አሰፋ እና በረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፤ በዚህ ኦሎምፒክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴቶች እርምጃ ውድድር ላይ ተሳትፈናል፡፡
ከተጀመረ 120 ዓመታትን ባስቆጠረበት የሪዮ ዴ ጄ ኔሮ 31ኛ ኦሎምፒያድ 17 ሴት እና 18 ወንድ አትሌቶችና አካቶ በስምንት የአትሌቲክስ የውድድር ተግባራት የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ቡድን በብርቅዬዋ አትሌት አልማዝ አያና በ10,000 ሜትር በተመዘገበ የወርቅ ሜዳልያ እና በሌሎች ሁለት የብር እና አምስት የነሃስ ሜዳልያዎች በማግኘት ከዓለም ዘጠነኛ፣ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
አልማዝ አያናና ሪዮ ዲጄኔሮ፡-
በሰባት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው በሄንግሎ ትሪያል 30:07.00 ፈጣን ሰዓት ባለቤት አልማዝ አያና፣ የ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ እና የ10,000 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼርዮት በርቀቱ በሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ ተፋጠዋል፡፡
ውድድሩ 37 ሴቶችን አካቶ በኬንያዊቷ አሊስ አፕሮት ናዋውና መሪነት ተጀመረ፡፡ ናዋውና ፍጥነት በመጨመር ዙሩን አከረረችው፤ ብዙዎቹ ተፎካካሪዎች ከቡድኑ እንዲቆረጡ አደረገች፤ ከአምስት ዙር በኋላ ከፊት ለፊት ስምንት አትሌቶች ወጡ፤ ሶስት ኬንያውያን (ናዋውና፣ ቼሩዮት እና ቤቲ ሴና)፣ ሶስት ኢትዮጵያውያንም (አልማዝ አያና፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ገለቴ ቡርቃ) አብረው ነበሩ፡፡
አልማዝ አያና አስራ ሁለት ዙሮች ሲቀሩ በድንገት ከፊት በመውጣት ግንባር ቀደም በመሆን ረጋ ብሎ ይሄድ የነበረውን ዙር አከረረችው፤ ቡድኑንም መበታተን ጀመረች፡፡
አልማዝ አያና እያንዳንዱን ዙር ከ71 ሰከንድ በታች መሮጥ ጀመረች፤ ከ12ኛዉ ዙር በኋላ ያሉትን ቀሪ ዙሮች እጅግ በሚያስገርም የአሯሯጥ ብቃት ብቻዋን ሮጣ በ29፡17.45 በሆነ ሰዓት የዓለምን ክብረ ወሰንን በማሻሻል አሸነፈች፡፡ በዓለማችን ባለፉት ኦሎምፒኮች ያልታየ፣ ያልተገመተ፣ ልዩ ክስተት አልማዝ ስትሮጥ ማንኛውም የስፖርት ሳይንስ ሊተነትነው በማይሞክረው ልዩ ብቃት ዓለምን ግራ አጋብታ በሚገርም ብቃት አሸነፈች፡፡
ቪቪያን ቺርዮት ሁለተኛ ስትሆን የለንደን ሻምፒዮኗ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የነሃስ ሜዳልያ ወሰደች፡፡ አልማዝ አያና በዚህ ውድድር ከዓለምና ከኦሎምፒክ ሪከርድ ሰዓት በተጨማሪ በድምሩ ስምንት ብሔራዊ ሪኮርዶችንም መስበር ችላለች፡፡ ሜዳልያቸውንም በኢትዮጵያዊቷ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በሆኑት በወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ የተበረከተላት ሲሆን የአበባ ስጦታ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንት በሎርድ ሰባስቲያን ኮይ እጅ ተበርክቶላታል፡፡
አልማዝ አያና የጥሩዬን የቤጂንግ ኦሎምፒክ ሁለት ወርቅ ሜዳልያ ለመድገም በ5,000 ሜትር ሴቶች ውድድር ተሳትፋ በኬንያውያኑ ቪቪያን ቺርዮት እና ሄለን ኦቢሪ ተቀድማ የነሃስ ሜዳልያን አስመዘገበች፡፡ ህልሟም እውን ሳይሆን ቀረ፡፡
ነገር ግን በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ያገኘቸው ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ በጀግናዋ አትሌት አልማዝ አያና የተመዘገበው ነበር፡፡
ሌሎች የተመዘገቡ ሜዳልያዎች፡-
ከ79 ሃገራት የተውጣጡ 150 አትሌቶች በተሳተፉበት የወንዶች ማራቶን ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ ሲያሸንፍ ከሱ አንድ ደቂቃ ዘግይቶ ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሌሊሳ 2፡09፡54 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያ አስመዘገበ፡፡ በ1,500 ሜትር ሴቶች ገንዘቤ ዲባባ በ4:10.27 በሆነ ሰዓት ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ወሰደች፡፡ ታምራት ቶላ በ10,000 ሜትር ወንዶች፣ ማሬ ዲባባ በማራቶን ሴቶች፣ ሃጎስ ገ/ሕይወት በ5,000 ሜትር ወንዶች ሶስት የነሃስ ሜዳልያዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን በአጠቃላይ ሪዮ ላይ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ አንድ ወርቅ፣ ሁለት ብር እና አምስት የነሃስ፣ በድምሩ ስምንት ሜዳልያዎችን በማግኘት ከአፍሪካ ሶስተኛ ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ኦሊምፒኩን አጠናቃለች፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from