ይህ እለት ቅዳሜ ህዳር 12/2013 ዓ.ም. ለንደን ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ2012 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሐምሌ 20 እስከ ነሃሴ 06/2004 ዓ.ም. በታላቋ ብሪታንያ ለንደን ከተማ ለ30ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 17 ወንድ እና 14 ሴት አትሌቶች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ርቀቶች፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የለንደንን የአየር ንብረት መሰረት ባደረገ ሁኔታ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ባሉ ከተሞች በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ይልማ በርታ፣ ሱ/ኢ ሁሴን ሼቦ፣ ንጉሴ ጌቻሞ፣ ብዙነህ ያኢ፣ መላኩ ደረሰ እና በረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
ሴቶች አትሌቶቻችን በውጤት ይበልጥ ጎልተው የወጡበት በታላቋ ብሪታኒያ ለንደን ከተማ የተካሄደው 30ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ከተመዘገቡት 8 ሜዳልያዎች መካከል ስድስቱ በሴት አትሌቶች የተመዘገቡ በመሆናቸው ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሶስቱ የወርቅ ሜዳልያዎች በጥሩነሽ ዲባባ 10,000 ሜትር፣ በመሰረት ደፋር 5,000 ሜትር እና በቲኪ ገላና ማራቶን ሲሆኑ ከነዚህም በተጨማሪ 2 ብር እና 3 ነሃስ፣ በድምሩ 8 ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ በኦሊምፒኩ ላይ በአትሌቲክስ ከተሳተፉ እና በሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ ከገቡ 42 ሃገራት መካከል ከዓለም 5ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችለናል።
መሰረት ደፋር፡-
በለንደኑ የ5,000 ሜትር የሴቶች ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን መሰረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ገለቴ ቡርቃን ለፍፃሜ አሰልፎ ውድድር ማስጀመሪያ ስፍራው ላይ ተገኘ፡፡ ወድድሩን የታላቋ ብሪታኒያ አትሌት ጆአን ፓቬይ የመጀመሪያዎቹን አራት ተከታታይ ዙሮች መራች፤ ጥሩነሽ አራተኛውን መስመር ይዛ ትሮጣለች፤ ከአራት ዙሮች በኋላ ኤሌና ሮማጎኖሎ ለጥቂት ዙሮች የፊት ለፊቱን ቦታ ያዘች፤ በኋላ እንደገና ፓቬይ ተቀበለቻት፤ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀር ጥሩነሽ ወደ ፊት ተስፈነጠረች፤ ከጀርባ መሰረት ተከተለቻት፤ የመቶ ሜትር መነሻ ላይ መሰረት የፊተኛውን መስመር ይዛ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት በ5,000 ሜትር በኦሎምፒክ 15:04.25 በሆነ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ አጠለቀች፤ይህ ውድድር የጀግናዋ መሰረት ልዩ ብቃት፣ እልህና የማሸነፍ አቅም የታየበት ልዩ መድረክ ነበር፡፡ መሲ ከጨረሰች በኋላ እልኋን ማብረድ አቅቷት በደስታ ሲቃ ትወራጭ ነበር፡፡ ጥሩነሽ በግምት በሶስት ሜትሮች ርቀት በኬንያዊቷ ቪቪያን ችርዮት ተቀድማ የነሃስ ሜዳልያ አገኘች፡፡ የመሲ አጨራረስ ብቃት እስከ አሁን ከብዙዎች አእምሮ አይጠፋም፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ፡-
ውድድሩ ተጀመረ በ10,000 ሜትር ሴቶች ሜዳልያ የማግኘት ድሉን ላለማስደፈር የኢትዮጵያ ሴቶች ቡድን ወደ ትራክ አቀና፤ ነገር ግን በጥሩነሽ ከፍተኛ ህመምና በነበራት የዝግጅት ማነስ ምክንያት የብዙዎች ግምት መንታ መንገድ ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ውድድሩ የተጀመረው በሦስቱ የጃፓን ሯጮች መሪነት ሲሆን ከመጀመሪያዎቹ 8 ዙሮች በኋላ ሌሎች ሯጮችን በማስከተል የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ወደ ፊት መጡ፡፡ ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን በመቀባበል ዙሩን አከረሩት፤ በተለይ በቡድን ሥራ ኬንያውያንን ለመቁረጥ የወርቅነሽ ኪዳኔ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ወርቅነሽ ኪዳኔ የምትታወቅበት የውድድር ባህሪዋ ለቡድን ስራ ያላትን ሁሉ የምትሰጥ ሃገር ወዳድና ጀግና በመሆኗም ጭምር ነው፡፡ ልክ እንደ ተለመደው 600 ሜትር ሲቀር ጥሩዬ ሁሉንም ጥላ ተፈተለከች ችርዮት ለመከተል ጥረት ብታደርም ሳይሳካላት ቀረ፤ በድንቅ አጨራረስ የቤጂንግን ኦሎምፒክ የ10ሺ ሜትር ድል ደገመችው፡፡ ጥሩዬ ህመሟን ችላ፣ የስልጠና እጥረቷን ተቋቁማ ለውድ ሃገሯ እስከ ሞት ድረስ የትጋፈጥ ጥቁር ፈርጥ ናት፡፡ ሌሎች የቡድን አጋሮቿ ወርቅነሽ ኪዳኔና በላይነሽ ኦልጂራ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡
ቲኪ ገላና፡-
በለንደን ከተማ እንብርት ላይ መነሻውንና መድረሻውን ባደረገው የሴቶች የማራቶን ውድድር ሃገራችን ኢትዮጵያ በቲኪ ገላና፣ በማሬ ዲባባ እና አሰለፈች መርጋ ተወክላ ተገኘች፤ የውድድር አሸናፊነት ቅድሚያ ግምት ለቲኪ አልተሰጠም ነበር፡፡ ዝናባማ በሆነ አየር የተጀመረው ማራቶን አስከ 12 ኪ.ሜ. ድረስ ማንም አትሌት ከፊት ሆኖ ለመምራት አልደፈረም፤ የዝናቡ መጠን እየቀነሰ ሲመጣ የተወሰኑ አትሌቶች ወደ ፊት መውጣት ጀመሩ፤ በውድደሩ አጋማሽ ላይ ቲኪ ውሃ ለመውሰድ ስትሞክር ተጠልፋ ወደቀች፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ቆረጡ፤ ነገር ግን በእልህና በቁጭት ተነስታ ውድድሯን ቀጠለች፡፡ 28 ኪ.ሜ. ላይ ሶስት ኬንያውያን እና ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ቲኪ ገላና እና ማሬ ዲባባ እየተፈራረቁ መሩት፤ የመጨረሻዎቹን ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሁለት ኬንያውያን፣ አንድ የሩስያ አትሌት እና ቲኪ ገላና ብቻ ተያያዙት፤ ውድድሩ ሊጠናቀቅ በግምት 1,500 ሜትሮች ያህል ሲቀሩ ያልተጠበቀችው ቲኪ ገላና ከፊት ተከሰተች፡፡ በድንቅ አጨራረስ የኦሎምፒክ ሪከርድ በሆነ 2:23:07 ሰዓት ከ1996 የአትላንታው የፋጡማ ሮባ ድል በኋላ ለሃገሯ ሁለተኛውን በኦሎምፒክ የሴቶች ማራቶን ወርቅ ሜዳልያ አስመዘገበች፡፡ ዝምታ በሚያጠቃትና በቁመተ ለግላጋዋ ቲኪ ገላና የማራቶን ወርቅ ከ16 ዓመታት በኋላ ለሃገራችን የተመዘገ ነበር፡፡
ሌሎች የተመዘገቡ ሜዳልያዎች፡-
በ3,000 ሜትር መሰናክል በሞስኮ 1980 በሻ/ል እሸቱ ቱራ ከተገኘ የነሃስ ሜዳልያ ውጭ ለሃገራችን ውጤት ያስመዘገበ አትሌት አልነበረም፤ በለንደኑ ኦሎምፒክ ሶፊያ አሰፋ የነሃስ ሜዳልያ አግኝታ የነበረች ብትሆንም በዶፒንግ ምክንያት አሸናፊ የነበረችው የሩስያ አትሌት ውጤት ተሰርዞ በሽግሽግ የብር ሜዳልያ በማግኘት በ3,000 ሜትር መሰናክል ለሃገሯ ሁለተኛ ሜዳልያ አስመዘገበች፡፡ በ5,000 ሜትር ደጀን ገ/መስቀል በአጨራረስ ስህተት በሞ ፋራህ ተቀድሞ የብር ሜዳልያ አገኘ፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ታሪኩ በቀለ የ10,000 ሜትር የነሃስ ሜዳልያ ሲያገኝ አበባ አረጋዊ በ1,500 ሜትር 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀው የነበሩት የቱርክ አትሌቶች ውጤት በዶፒንግ ቅሌት በመሰረዙ ምክንያት በደረጃ ሽግሽግ የነሃስ ሜዳልያ ወሰደች፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from