ይህ እለት አርብ ህዳር 11/2013 ዓ.ም. በቤጂንግ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ2008 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከነሃሴ 02-18/2000 ዓ.ም. በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ለ29ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 14 ወንድ እና 13 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የቤጂንግ በጣም ልዩና አደገኛ ሙቀትና፣ ወበቅና የአየር መበከል ያለበት በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በደብረ ዘይት ሆራና በአዋሽ መልካሳ አካባቢ በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ፣ ዶ/ር ይልማ በርታ፣ ሻምበል ዘላለም ደስታ፣ ሻምበል ዮሐንስ መሃመድ እና በረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ጥሩነሽና ቀነኒሳ በድርብ ወርቅ የተንቆጠቆጡበት፣ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የጀግናውን ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ድርብ ድል በሁለቱም ፆታ እንደ ገና ለዓለም ገሃድ ያሳዩበት እንዲያውም በቤጂንግ የወፍ ጎጆ ስታዲየም ሲፈነጩ የከረሙበት መድረክ ነበር፡፡ ሁለት፣ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡበት፣ በኦሎምፒያዱ ላይ የተገኙት አራቱ የወርቅ ሜዳልያዎች በእነዚሁ አትሌቶች ከመሆኑም ባሻገር ከሲድኒ ኦሎምፒክ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በድል ካሸበረቀችባቸው ኦሎምፒኮች መካከል በመጀመሪያዎቹ ተርታ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡
ቀነኒሳ በቀለ፡-
ለ2ኛ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ የተሳተፈው ስመ ገናናው ቀነኒሳ በቀለ በአቴንስ ኦሎምፒክ የሞስኮን የምሩፅን የሁለት ወርቅ ገድል ሞክሮ በ5ሺ ሜትር ብር በማግኘቱ እድሉ አመለጠው ሆኖም ግን በቁጭት አራት ዓመታትን በጠንካራ ልምምድ እና ኢትዮጵያዊ ቁጭት ታግዞ ቤጂንግ ላይ ህልሙን አሳካ፡፡ በሃገሩም አዲሱ ተተኪ ድንቅ ተብሎ ተሰየመ፡፡
ቀነኒሳ የቡድን አጋሮቹን ስለሺ ስህን እና ኃይሌ ገ/ስላሴን አሰልፎ በ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከመሮጫ መሙ ላይ ታየ፤ በወቅቱ በነበረው የስነ ልቦናና አካላዊ ብቃት ዝግጅቱ ውድድሩን እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነበር፡፡ ዙሩን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ተጓዘ፤ የመጨረሻውን ዙር በ53.42 ሰከንድ ሮጦ የኦሎምፒክ የ10ሺ ሜትር ሪከርድን ጭምር በመስበር 27፡01.17 በሆነ ሰዓት አሸነፈ፡፡ ሌላው የሃገሩ ልጅ ስለሺ ስህን ቀነኒሳን ተከትሎ ለሃገሩ የብር ሜዳልያን አስመዘገበ፤ ኃይሌ ገብረስላሴ 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፤ ለቀነኒሳ ውጤት መሳካት በታክቲክና በቡድን ስራ አጋሮቹ ስለሺና ኃይሌ የነበራቸው ሚና የጎላ ነበር፡፡ በዚህም ኃይሌ ልዩ ተተኪዎችን እንዳፈራ ዓለም መሰከረ፡፡
በ10ሺ ሜትር ድል የተነቃቃው ንጉሱ ቀነኒሳ በ5ሺ ሜትር ውድድር ማጣሪያ አድርጎ ለፍፃሜ ውድድር ከታናሽ ወንድሙ ታሪኩ በቀለና ከሌላው የቡድን አጋሩ አብርሃም ጨርቆሴ ጋር ውድድሩን በመተጋገዝና በቡድን ስራ ተያያዙት፤ እንደ ተለመደው በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃት የ5ሺ ሜትርን ድል የኦሎምፒኩን ሪከርድ ጭምር በመጨበጥ በ12፡57.82 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ወርቁን አጣጣመ፡፡ ቀነኒሳ በቤጂንግ 5000 ሜትር ውድድር ዘጠኝ ዙሩን በመምራት ያሳየው ልዩ ብቃት እስካሁን ማንም ሊሞክረው የማይችል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የቀነኒሳን የቤጂንግ ድል ልዩ የሚያደርገው ከ28 ዓመታት በፊት በሞስኮ ኦሊምፒክ የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ድልን ያስታወሰን ከመሆኑም በላይ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሪከርዶችንም በመስበር ጭምር ያሸነፈበት በመሆኑ ነው፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ፡-
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በተደረገው የ10ሺ ሜትር ውድድር በ29:54.66 በሆነ ሰዓት በመግባት በውድድሩ አንደኛ በመውጣት አዲስ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ባለቤት ለመሆን በቃች። የውድድሩ መጀመሪያ አጋማሽ ዙሮች በኔዘርላንዳዊቷ ሎርና ኪፕላጋት የበላይነት ቀጠለ፡፡ ነገር ግን በውድድሩ አጋማሽ ተፎካካሪዎቹ በኤልቫን አብይ ለገሰ መሪነት ወደ ፊት ተምዘገዘጉ፤ ቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች ከኋላዋ ተሰለፉ፡፡ በውድድሩ መገባደጃ አካባቢ ጥሩዬ እንደ ተለመደው ከፊት ብቅ አለች፤ በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃት በሲድኒ ኦሎምፒክ በአክስቷ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተይዞ የነበረውን የኦሎምፒክ ሪከርድ 29፡54.66 በሆነ ሰዓት አሻሽላ ወርቅ ሜዳልያውን ለሃገሯ በማስመዝገብ ገድሏን አንድ ብላ ጀመረች፡፡ በቤጂንግ የተመዘገበው ሰዓት ለአፍሪካ ፈጣኑ ክብረ ወሰን ነው። ብዙ የማትናገር ሁሌም ለስለስ ያለ ፈገግታ የማይለያት፣ ድንቅ፣ ስትራመድ ኮራ ያለች ልዩ ብርቅ፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ በ5ሺ ሜትር መሰረት ደፋርን ቀድማ በመግባት 15:41.40 በሆነ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ለመሆን በቃች። በዚህ ኦሎምፒክ በሁለት ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘቷ በአለም የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ሆናለች። በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር በአንድ ኦሎምፒክ አሸናፊ የሆነች እንስት ከጥሩነሽ ውጭ የለም፡፡
የ5ሺ ሜትር የሴቶች ውድድር በስልታዊነቱ ይህ የተለየ ቢሆንም ውጤቱ ከሳምንት በፊት ከነበረው የ10ሺ ፍፃሜ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ ንግስቷ ጥሩነሽ ዲባባ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያዋን አጠለቀች፡፡ በውድድሩ ላይ ኤልቫን አብይ ለገሰ ቀድማ መሪ ሆና ብትቆይም ኬንያውያን መሪነቷን ተረክበው ወደ ፊት አቀኑ፤ ዙሩ እየከረረ ሄደ፡፡ በመጨረሻው ዙር ላይ መሰረት ደፋር ወደ ፊት አፈትልካ ወጣች፤ ንግስቷ ተከተላቻት፤ በመጨረሻም በነበራት የአጨራረስ ብቃት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ 15፡41.40 በሆነ ሰዓት ወሰደች፤ መሰረት ደፋርም የብር ሜዳልያ ለሃገሯ አበረከተች፡፡
በሌሎች ውድድሮች፣
በማራቶን ፀጋዬ ከበደ ኬንያዊውን ሳሙኤል ዋንጅሩንና የሞሮኮውን ጃዋድ ጋሪብን ተከትሎ ብቸኛዋን በውድድሩ ላይ የተገኘ የነሃስ ሜዳልያ አጠለቀ፡፡ በዚህ ኦሊምፒክ በጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ አራት የወርቅ ሜዳልያዎች፣ በስለሺ ስህንና በመሰረት ደፋር በ10ሺ ሜትር ሁለት የብር ሜዳልያዎች እና የፀጋዬ የማራቶን ነሃስ ሜዳልያዎችን ጨምሮ በአትሌቲክስ ሃገራችን በድምሩ 7 ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ችላ ከዓለም 5ኛ፣ ከአህጉረ አፍሪካ 2ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from