ይህ እለት ሐሙስ ህዳር 10/2013 ዓ.ም. በአቴንስ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ2004 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከነሃሴ 07-23/1996 ዓ.ም. በግሪክ አቴንስ ከተማ ለ28ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 12 ወንድ እና 12 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በ3,000 ሜትር መሰናክል እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የአቴንስን የአየር ንብረት መሰረት ባደረገ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያና ደብረዘይት አካባቢ በተጨማሪም በአዳማና ሀዋሳ መንገድ በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ፣ ዶ/ር ይልማ በርታ፣ መ/አ ትዕዛዙ ውብሸት እና በረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
የመጀመሪያውን ኦሎምፒክ ያስተናገደች ግሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀቸው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በቀነኒሳ በቀለ እና በመሰረት ደፋር በተገኙ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች እና በሶስት ብርና ሁለት ነሀስ ሜዳልያዎች ከዓለም አምስተኛ ከአህጉረ አፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
የወንዶች 10 ሺ ሜትር ውድድር
የወንዶቹ 10 ሺ ሜትር ከመካሄዱ በፊት ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቀ ነው፤ ታላቁ ኃይሌ ገብረስላሴ በእውነቱ ድሉን እንደገና እውን ሊያደርገው ይችላል? ኢትዮጵያዊው የኦሊምፒክ ሻምፒዮንነትን 2 ጊዜ በማሸነፍ 4 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና ሆኖ በዓለም አትሌቲክስ አናት ላይ ከ10 ዓመታት በላይ ያሳለፈ ነበር፡፡ በአቴንስ ይሄንን ክብር ማስጠበቅ ይችላል? የሁሉም ጥያቄ ነበር፡፡
ውድድሩ ተጀመረ ሦስቱ የኢትዮጵያን የሃገራችን ውድና ብርቅዬ ወጣት አትሌቶች በልበ ሙሉነት እና በከፍተኛ ደረጃ የታክቲክ ምስጢራዊ ችሎታ ጀመሩት ፡፡ የሩጫውን የመጀመሪያ ሩብ ምቹ በሆነ ጊዜ ከሮጡ በኋላ ፍጥነቱን ጨምረው ሜዳውን መከፋፈል ጀመሩ ፡፡ ሩጫውን ከግማሽ በታች በሆነ ጊዜ ግማሽ ያህሉ ተፎካካሪ ከዋናወ የመሪዎች ፉክክር አስቀድሞ ወጣ፡፡
ኃይሌ ከቡድኑ የተወሰነ የራቀ ይመስላል እዚህ ውድድር ላይ እንደፈለገው እንዳይሮጥ ያገደው ከዚህ ቀደም በተደረጉ ውድድሮች ገጥሞት የነበረው የጉዳት ይዞ ነበር፡፡
ብዙ ተፎካካሪዎች በዙር ላይ በመንጠባጠባቸው ኃይሌ ከሁለቱ የሃገሩ ልጆች ፍጥነት ጋር ለመጣጣም ይታገል ነበር፡፡ ስለሺ እና ቀነኒሳ አብሮአቸው እንዲሮጥ በትንሹ የቀዘቀዙ ሲሆን ሶስት ዙር ሲቀረው ግን ከርሱ ተለያይተዋል፤ ፍጥነታቸውን ጨምረው እየተመሙ ነው፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና አትሌት ስለሺ ስህን ከኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ እና ከኡጋንዳዊው ቦኒፌስ ኪፕሮፕ ጋር የመጨረሻውን ዙር ተያያዙት፡፡ ሆኖም ተአምረኛው ቀነኒሳ በቀለ 27:05.10 በሆነ ሰዓት የሃገሩን ልጅ ስለሺ ስህንን አስከትሎ በድል ገባ፡፡ የኤርትራው ዘረሰናይ ታደሰ የነሃስ ሜዳልያ አገኘ፡፡ አይበገሬው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ለቡድን አጋሮቹ አሸናፊነት የነበረው ሚና የጎላ ቢሆንም ውድድሩን 5ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቀቀ፡፡ የ10 ሺ ሜትር የኦሎምፒክ አክሊሉንም ለንጉሱ ቀነኒሳ በቀለ አስረከበ፡፡
መሰረት ደፋር፡-
አትሌት መሰረት ደፋር በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ተካፍላ ለሃገሯ በርካታ ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ብትችልም በኦሊምፒክ የነበራት የመጀመሪያ ተሳትፎዋ የ5,000 ሜትር የአቴንስ ኦሊምፒክ ነበር፡፡ ውድድሩም ተጀመረ፤ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አንዳቸውም መሪነቱን መውሰድ አልፈለጉም፤ ውድድሩ በዝግታ ተጀምሯል፡፡
የቻይና አትሌቶች ሱን ይንግጂ እና ሺንግ ሁይና የመሪነቱን ቦታ ያዙ፡፡ ወደ ሩጫው አጋማሽ ምልክት ሲቃረቡ የቱርክ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኤልቫን አቢይ ለገሰ ቀዳሚ የነበሩትን ቻይናውያን በማለፍ ወደ መሪነት ፍጥነት በመጨመር አለፈች፡፡ መሰረት ደፋር እና ኬንያዊቷ ኢዛቤላ ኦቺቺ የመሪዋን እግር በመከታተል ወዲያው ወደ ፊት ከተፍ አሉ፡፡ ሶስት ዙሮች ሲቀሩ ኤልቫን አብይ ለገሰ፣ መሰረት እና ኦቺቺን በመተው ወደ ፊት ጥላቸው ተስፈነጠረች፤ የመጨሻው ዙር ደውል ሲደወል ኦቺቺና መሰረት ተከታትለው ወጡ፤ ኤልቫንንም አለፏት፤ 200 ሜትር ሲቀር መሰረት ያላትን የአጨራረስ ታክቲክ ተጠቅማ ኦቺቺን ጥላት ተፈተለከች፡፡ በኦሎምፒክ የመጀመሪያ በሆነ ተሳትፎዋ በ14፡45.65 በሆነ ሰዓት የኦሎምፒክ ክብርን ተቀዳጀች፤ ኬኒያዊቷ ኦቺቺ 2ኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ጥሩነሽ ዲባባ በ14:51.83 በሆነ ሰዓት የነሃስ ሜዳልያ አጠለቀች፡፡
ሌሎች ሜዳልያ የተገኘባቸው ውድድሮች፡-
የሴቶች 10,000 ሜትር የሲድኒ ኦሎም ባለድል ጀግናዋ ደራርቱ ቱሉ ከእህቷ ልጅ እጅጋየሁ ዲባባ እና ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ወርቅነሽ ኪዳኔ ጋር ተሰለፉ፤ በውድድሩ ቻይናዊቷ ሺንግ ሁይና ስታሸነፍ እጅጋየሁ ዲባባ 30፡24.98 በሆነ ጊዜ 2ኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳልያ አገኘች፤ ደራርቱ ቱሉ የነሃስ ሜዳልያውን ወሰደች፡፡
በ5,000 ሜትር ወንዶች በድጋሚ የተወዳደረው ቀነኒሳ በቀለ ለድርብ ድል የነበረው ተስፋ በሞሮኮው አትሌት ሂሻም ኤልጉሩዥ ተጨናግፎ በ13፡14.59 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያ አስመዘገበ፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from