ይህ እለት ረቡዕ ህዳር 09/2013 ዓ.ም. በሲድኒ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ2000 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከመስከረም 01-21/1993 ዓ.ም. በአውስትራሊያዋ ሲድኒ ከተማ ለ27ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 13 ወንድ እና 11 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በ3000 ሜትር መሰናክል እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የሲድኒን የአየር ንብረት መሰረት ባደረገ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙሪያና ደብረዘይት አካባቢ በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ፣ ዶ/ር ይልማ በርታ፣ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣ ሻምበል ዘላለም ደስታ እና በረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
የሲድኒ አየር ንብረት ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ ስለነበር በዚህም ጀግናው ቡድናችን ከመነሻው ታላቅ መንፈሳዊ አቅም አጎለበተ፡፡
የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ከተማ 27ኛውን ኦሎምፒያድ ስታዘጋጅ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከተካፈለችባቸው ኦሎምፒያዶች ሁሉ የተሻለውን ሜዳልያ ያስመዘገበችበት ነበር፡፡
በዚሁ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ 4 ወርቅ፣ 1 ብር እና 3 ነሃስ፣ በድምሩ 8 ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ በሜዳልያ ሰንጠረዥ አሜሪካንን ተከትላ 2ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነበር፡፡
አትሌቶቻችን በሲድኒ
በወጣቶች የተሞላው የአትሌቲክስ ኦሎምፒክ ቡድን ዝግጅቱን በአራራት ሆቴል በማድረግ የ3 ወራት የተለመደ ቆይታውን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች ደብረዘይትን ጨምሮ አከናወነ፡፡ ጠንካራና እልኸኛ የአሠልጣኞች ስብስብ በዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬና በዶ/ር ይልማ በርታ እየተመራ ዝግጅቱን በተያዘለት አግባብ አከናወነ፡፡ የሲድኒ አየር ንብረት ሁኔታ ከሃገራች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ሲድኒ ለአትሌቶቻችን ይከብዳል ተብሎ አልታሰበም፡፡
ነገር ግን የቡድኑ ልዩ ተስፋ የነበሩት ኃይሌና ደራርቱ በደረሰባቸው ከፍተኛ የጤና ችግር (የቋንጃና የቁርጭምጭሚት ህመም) ምክንያት መደበኛ ስራ መስራት መቸገራቸው በቡድናችን ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጠረ፡፡ ያልተሞከረ ህክምና የለም፤ ከአዲስ አበባ እስከ ሆላንድ ድረስ እስራኤልም ሀገር ቀጠሮ በዛ እንጂ ሊኬድ ነበር፤ ግን አልሆነም፤ ምን ይደረጋል ፈጣሪ ይጨመርበት ተብሎ ዝግጅቱ ቀጠለ፡፡ ያቺ የመሄጃ ቀንም ተቃረበች፤ በወቅቱ የስፖርት ኮሚሽን ተቀዳሚ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ መላኩ ጴጥሮስ ልዩ ስትራቴጂ ቀየሱ፤ ኃይሌም አልሄድም አለ፤ ነገር ግን እርሳቸው ሃገራዊ ግዴታቸውን ተወጡ፤ ኃይሌ ሲድኒ እንዲሄድ ተደረገ፡፡
ጊዜው የኃይሌና የደራርቱ መሆኑ እየቀነሰ መጣ፤ ለተሳትፎ እንደሚጓዙ ሁሉም በአዕምሮው ውስጥ ያዘ፤ ግን ሌሎች ልዩ ጀግኖች በድንገት እንደሚፈጠሩ ሁሉም ያምን ነበር፡፡
በሲድኒ በኃይሌና በደራርቱ ላይ የህክምና ርብርብ ተደረገ፤ የዓለም ሐኪሞች ሁሉ እነርሱን ለማገዝ ፍቃደኛ ሆኑ፤ ግን ቡድናችን ገና አልረካም ነበር፤ በተለይ ዶ/ር ወልደመስቀል፡፡ ጀግኖቹ ግን ማንም ሳያስብ በህልሙ ሳይታየው ለዳግመኛ ድል በድንገት አንድ ጠዋት ላይ በልምድ ላይ ተገኙ፤ በቡድንናችን አዲስ እና ልዩ መንፈስ መጣ፤ ሁሉም በስውር ፈገግ አለ፤ ፈጣሪንም አንጋጦ አመሰገነ፤ ግን ገና ነው፤ ምን ይፈጠር ይሆን በማለት ዝምታን መርጦ ነበር፡፡
ኃይሌ ገ/ስላሴ፣
በ10ሺ ሜትር ልዩ ጀግናው ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴና ኬንያዊውን ፓል ቴርጋት ዓለም ምንግዜም የማይረሳው ትንቅንቅ አሳይተዋል:: ሁለቱ አትሌቶች እስከ መጨረሻው የድል መስመር ተፎካክረው በ9 ማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት በመቅደም ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገብረስላሴ በ10ሺ ሜትር 27፡18.20 በሆነ ሰዓት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያውን ተጎናፀፈ፤ ኬንያዊው አትሌት ፖል ቴርጋት 2ኛ ደረጃ ሲይዝ ሌላው ድንቅ ኢትዮጵያዊው አትሌት አሰፋ መዝገቡ 3ኛ ደረጃን ይዞ ፈፀመ፡፡ በዚህ ኦሎምፒክ ኃይሌ አጋጥሞት በነበረው ህመም የተነሳ ከተሳትፎ በዘለለ የጠበቀው አልነበረም፤ ነገር ግን ህመሙን ተቋቁሞ ለሃገሩ ክብር ራሱን መስዋዕት በማድረግ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር አሸናፊነትን ተቀዳጀ፡፡
ደራርቱ ቱሉ
የ10ሺ ሜትር ውድድር ተጀመረ፤ የሁሉም ዓይን ጌጤ ላይ አተኮረ፤ ግን ደራርቱ ህመሟን ችላ አምላኳን እየተማጸነች ውድድሩን ተቆጣጥራ ጀግናዋ ቢሆንላት ድሉን ለሃገሯ ልትደግም ካልሆነም የቡድን አጋሮቿን ልታግዝና መስዋዕትነት ልትከፍል መጓዟን ቀጠለች፡፡ ውድድሩ ለመገባደድ ተቃርቧል፤ የሩጫው ዙር ከረረ፤ በፊት የሚያስገመግመው ቡድን ደራርቱን ጥሎ ለመሄድ ሙከራ አደረገ፤ ይህም ተሳካና በመሀላቸው ክፍተት ተፈጠረ፤ ሁሉም አጎነበሰ፤ ጀግናችን ቀረች አለ፤ አይኖች ዕንባዎችን በድንገት አዘሉ፤ ፈጣሪውን ወደ ላይ ተማፀነ፤ በቅፅበት ግን ወደ ትራኩ መለስ ሲባል ማመን የሚያቅት ነገር ተፈጠረ፤ ደራርቱ ከጌጤ ጎን ተገኘች፤ ሲድኒ እንደ ጮራ ፈነጠቀች፡፡ ደራርቱ ቱሉ በአስደናቂ የአሯሯጥ ውበት በ10ሺ ሜትር ሁለተኛውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ወሰደች፡፡ መቼም የማይታመን ልዩ ችሎታ፡፡
ገዛኸኝ አበራ
በሲድኒ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር በሁለት ኢትዮጵያውያን ገዛኸኝ አበራ እና ተስፋዬ ቶላ ከኬንያዊው ኤሪክ ዌይንኔይ ጋር ፉክክሩ ተቀጣጠለ፡፡ ወደ 37ኛው ኪሜ ሲደርሱ ኬንያዊው ኤሪክ ዌይንኔይ ሁለቱን ለመቁረጥ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ከ 2 ኪ.ሜ በኋላ የ22 ዓመቱ ወጣት ገዛኸኝ አበራ መሪነቱን በመያዝ ወደ መጨረሻው መስፈንጠር ጀመረ፡፡ ይህ ዕድሜ ዣን ካርሎስ ዛባላ እ.ኤ.አ. በ1932 በሎስ አንጀለስ ከተወዳደረበት ዕድሜ ቀጥሎ የተገኘ ወጣቱ ማራቶን ሯጭ ያደርገዋል፤ ውድድሩንም በሚያስገርም ብቃት በ2:10:11 በሆነ ጊዜ በአንደኛነት ጨረሰ፤ ይህ ከማሞ ወልዴ ሜክሲኮ ኦሎምፒክ አሸናፊነት በኋላ የተገኘ ልዩና ድንቅ ድል ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ከ32 ዓመታት በኋላ የማራቶንን ክብር ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ የበቃው በገዛኸኝ አበራ የወርቅ ሜዳልያ ድል ነበር፡፡ ለሃገሩ ልዩ ትዝታ አዘል ድል አበሰረ፡፡
ሚሊዮን ወልዴ
ወጣቱና የ22 ዓመቱ ሚሊዮን ወልዴ ብቃት ጎልቶ የወጣው በ2000 ሲድኒ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በ5,000 ሜትር ሲሳተፍ ነበር፡፡ ሚሊዮን ወልዴ ብዙም ፈጣን ባልነበረው ውድድር ከኋላ ካደፈጠ በኋላ ለፍጻሜ ሁለት መቶ ሜትር ሲቀረው መሪዎቹን አልጄሪያዊው አሊ ሳዲ ሲኢፍ እና የሞሮኮው ኢብራሂም ላህፍን ተስፈንጥሮ በመውጣት በ13:35.49 ሰዓት አሸናፊ ለመሆን በቃ፡፡ ለማመን የሚያስቸግር የወጣት ኢትዮጵያዊ ድል፡፡
በሲድኒ የተገኙ የብርና የነሃስ ሜዳልያዎች፤
ጀግናዋ አትሌት ጌጤ ዋሚ በአትላንታ ካገኘችው ነሃስ ቁጭት በኋላ በ10 ሺ ሜትር በሲድኒ ህመማዋን ችላ በድል የተወጣችውን ደራርቱን ተከትላ የብር ሜዳልያ አገኘች፤ በ5ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳልያ አገኘች፡፡ አሰፋ መዝገቡ በ10 ሺ ሜትር አስከ መጨረሻው ተጋድሎ በሃገሩ ልጅ ኃይሌ እና በኬንያዊው ቴርጋት ተቀድሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳልያን ለሃገሩ አስመዘገበ፡፡ ሌላው በማራቶን ሃገራችንን የወከለው አትሌት ተስፋዬ ቶላ የነሃስ ሜዳልያን ሲያገኝ ገዛኸኝ አበራን እና ኬንያዊውን አትሌት ኤሪክ ዌይንኔን ተከትሎ በመግባት ነበር፡፡
ምንጭ ፡- የዶ/ር አያሌው ጥላሁን የጉዞ ማስታወሻ እንደ ምንጭነት ተጠቅመናል
Similar Posts
Latest Posts from