ይህ እለት ማክሰኞ ህዳር 08/2013 ዓ.ም. በአትላንታ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1996 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሃምሌ 12-28/1988 ዓ.ም. በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ለ26ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 8 ወንድ እና 8 ሴት አትሌቶች በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀቶች እና በማራቶን ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የአትላንታን ሞቃታማና ወበቃማ የአየር ንብረት መሰረት ባደረገ የሃገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ ልምምድ በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ እና በረዳቶቻቸው ዶ/ር ይልማ በርታና ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
እ.አ.አ በ1996 በአሜሪካዋ አትላንታ ከተማ የተካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ከ28 ዓመት በፊት በወንዶች ማራቶን በማሞ ወልዴ ሜክሲኮ ላይ ከተገኘው ድል በኋላ ለአፍሪካም ጭምር የመጀመሪያ የሆነውን የሴቶች የማራቶን ድል በጀግናዋ አትሌት ፋጡማ ሮባ ገድል የተመዘገበበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ኦሎምፒክ በወጣቱ አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ የ10,000 ሜትር ድል የምሩፅ ይፍጠርን የሞስኮ ገድል ያስታወሰ ሲሆን ጌጤ ዋሚም በ10,000 ሜትር ሴቶች ውድድር ለሃገሯ ነሃስ ሜዳልያ ያስመዘገበችበት ኦሎምፒክ፡፡
ኃይሌ ገ/ስላሴና ፋጡማ ሮባ በአትላንታ
ኃይሌ ገ/ስላሴ፡-
ኃይሌ አብዛኛውን ጊዜውን ለአትላንታ ኦሎምፒክ ዝግጅት ያደርግ ነበር፤ የልጅነት እድሜው ጀግና የነበረውን እና ወደ ሩጫ ተስቦ እንዲገባ ያረገውን የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የሞስኮ የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ገድል መድገም ህልሙ ነበር፡፡ በአትላንታ ኦሎምፒክ በ10,000 ሜትር ሩጫ እስከ መጨረሻው ዙር ድረስ ኬንያዊውን አትሌት ፖል ቴርጋትን ተከትሎ ከሮጠ በኋላ በመጨረሻው ዙር ባለው አስገራሚ የአጨራረስ ብቃት ተጠቅሞ በመስፈንጠር ቴርጋትን ቀድሞ በኦሎምፒክ በነበረው ተሳትፎ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በ27፡07.34 የኦሎምፒክ ሪከርድ በሆነ ሰዓት ሲያሸነፍ ብርቱ ተፎካካሪው ቴርጋት ሁለተኛ፣ የሞሮኮው ሳላህ ሂሱ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀቁ፡፡
ኃይሌ በአትላንታ ኦሎምፒክ የ10 ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሪኮርድ በመስበር አሸንፎ የርቀቱን ክብር ከሶስት ኦሎምፒኮች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሰው ችሏል፡፡ በአትላንታ የነበረው ደረቅ የመሮጫ መም በ10,000 ሜትር በሮጠበት ጊዜ የመጨረሻዎቹ ዙሮች በነበራቸው ፍጥነት የተነሳ ኃይሌ እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በ5,000 ሜትር ሳይሳታሰፍ ቀረ፡፡ በዚህም የምሩፅን ታሪክ ለመድገም የነበረው ህልም ተጨናገፈ፡፡
ፋጡማ ሮባ
በ1960 በክቡር ዘበኛው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ፈር ቀዳጅነት የተጀመረው የኦሎምፒክ የማራቶን ድል የኢትዮጵያ ባህል ሆኖ ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት በቶኪዮ በራሱ በአበበ፣ በሜክሲኮ በሻምበል ማሞ ወልዴ ድል በኋላ ይህው ድል ለ28 ዓመታት ከኢትዮጵያ ከራቀ በኋላ እንደ ተለመደው የወንዶቹ የማራቶን የአፍሪካ ፈር ቀዳጅነት ድል በሴቶች የማራቶን ሮጫ በ1996 የአትላንታ ኦሎምፒክ በ23 ዓመቷ ወጣት አትሌት ፋጡማ ሮባ እጅ ሰጠ፡፡
ፋጡማ ሮባ የመጀመሪያውን ማራቶን ፈር ቀዳጅ ድሏን እ.ኤ.አ. በ1996 በሞሮኮ ማራክሽ አጣጣመች፣ በመቀጠልም ከሁለት ወር በኋላ የሮምን ማራቶን አሸናፊ ሆነች። በሁለቱ ማራቶኖች መካከል የግል ሰዓቷን በጥሩ ጊዜ አሻሽላለች፡፡ ከሮም አሸናፊነት በኋላም ወጣቷ አትሌት በ1996 በአትላንታ አሜሪካ በሚደረገው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡድን የተመረጠች ሲሆን ስልጠናዋን አጠናክራ ቀጠለች፡፡ በአትላንታ ኦሎምፒክ በሴቶች ማራቶን ውድድር ከ18 ኪ.ሜ (11 ማይል) ከሮጠች በኋላ በድንገት ከቡድኑ ተስፈንጥራ በመውጣት መምራት ስትጀምር በነበራት የአካል ብቃት ውድድሩን እንደምታሸንፍ እርግጠኛ መሆኗን ተናግራለች፡፡ ውድድሯንም በ2:26:05 በሆነ ሰዓት አንደኛ በመሆን አጠናቀቀች፡፡ ፋጡማን በመከተል ሁለት ደቂቃ ዘግይተው የሩስያዋ ቫለንቲና ይጎሮቫና ጃፓናዊቷ ዩኩ አርሞሪ 2ኛና 3ኛ በመሆን ተከታትለው ገቡ፡፡ አህጉረ አፍሪካ የመጀመሪያውን የሴቶች የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ለዚያውም ሙቀቱና የአየር ርጥበቱ በጣም ገኖ በታየበት የአትላንታ በረሃ በአይበገሬነት ኢትዮጵያዊትና አፍሪካዊት ወጣት ለግላጋ አትሌት ፋጡማ ሮባ አማካይነት አጠለቀች፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from