ይህ እለት ሰኞ ህዳር 07/2013 ዓ.ም. በባርሴሎና ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1992 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሃምሌ 18 እስከ ነሃሴ 03/1984 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና ከተማ ለ25ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 9 ወንድ እና 6 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በማራቶን እና እርምጃን ጨምሮ ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች የባርሴሎናን የአየር ንብረት መሰረት ያደረገ በተያዩ የሃገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ ልምምድ በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት በአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ እና ረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
የሮም የአበበ ድል በ25ኛው የባርሴሎና ኦሎምፒያድ ለኢትዮጵም ሆነ ለአፍሪካ በሴቶች በፍልቅልቋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ በ10,000 ሜትር የተመዘገበበት በመሆኑ ባርሴሎናንም ሆነ የፍልቅልቋን አትሌት ታሪክ በወርቅ ፅፎ መቼም አይረሳቸውም፡፡
በባርሴሎና ፊጣ ባይሳ በ5000 ሜትር የነሃስ ሜዳልያ ሲያገኝ በ10000 ሜትር 9ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊው ሀዲስ አበበ በ5000 ሜትር ማጣሪያውን ሳያልፍ ቢቀርም በ10000 ሜትር ነሀስ ሜዳልያን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በዚህም በደራርቱ በተገኘ አንድ ወርቅ እና በፊጣና ሀዲስ ባስመዘገቡት ሁለት የነሃስ ሜዳልያዎች በኦሎምፒኩ ከተሳተፉ ሃገራት በአትሌቲክስ ከአፍሪካ 3ኛ ከዓለም 12ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች፡፡
ባርሴሎናና አትሌት ደራርቱ ቱሉ
የ1992 ባርሴሎና ኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር የሴቶች ውድድር የኢትዮጵያ ቡድን በወጣቷ ደራርቱ ቱሉ እየተመራ ትዕግስት ሞረዳንና ሉቺያ ይስሃቅን አካቶ በዚያ የሙቀት ነበልባል በሚታፈነው ስታድዮም ብቅ አለ፡፡ ቁጭት፤ ስጋት፤ ኢትዮጵያዊነት ሁሉሙ ባንድ ላይ ተዳምረው ቡድናችንን ወጥረው ይዘውታል፡፡ ይገርማል ከሙቀቱ ከፍተኛነት የተነሳ በትራኩ በካታንጋ በኩል የውኃ መጠጫዎችና ስፖንጆች ተዘጋጅተዋል፡፡ የማስነሻው ጥይት ተተኮሰ፤ ውድ የሃገራችን ብርቅዬ ልጆች እሳተ ገሞራውን ተያያዙት፤ ልዑካኑ በጭንቀት ተውጧል፤ የረጅም ርቀት አሰልጣኙ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ዝምታን መርጠው በአንክሮ ውድድሩን ይመለከታሉ፤ አንድ ለግላጋ ወጣት ከመሪዎቹ ጋር ተቀላቅላ፤ ከደቡብ አፍሪካዊቷ ሄሊና ሚየር ጀርባ በመሆን በዝምታ ትወነጨፋለች፡፡ ወጣቷ ኢትዮጵያዊት ውኃ እንኳን አትወስድም፤ ቢጮሁ አትሰማም፣ ዝም ብላ ትገሰግሳለች፤ ከውድድሩ ትንሽ ቀናት በፊት በጠና ታማ በብዙ የህክምና ርብርብ ነው ለውድድሩ የደረሰችው፡፡ ውድድሩ ሊያልቅ ነው፤ ዓለም ሁሉ መጨረሻውን አፍጥጦ ይከታተላል፤ ሁለት አፍሪካውያን ብቻቸውን ወደ ፊት ተስፈነጠሩ፤ በዚያ እሳተ ጎሞራ ይንቀለቀላሉ ዝምታው፤ መንቀጥቀጡ በረታ፤ ውድድሩ ሊያልቅ አንድ ዙር ብቻ ቀረው፤ ድንገት የመጨረሻው ዙር ሊጀመር ሲል አንዲት ልዩ፤ ድንቅ ለግላጋ መሪነቱን ከደቡብ አፍሪካዊቷ ተቀበለች፤ ውድ ሃገሯን ልታኮራ፤ አፍሪካን፤ ጥቁሮችን ወደ ሰንደቅ ልታወጣ፤ በልዩ ኢትዮጵያዊነት ወኔ ያንን ትራክ ተምዘገዘገችበት፤ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ መቼም የማይረሳውን የበረሃ ገድል ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ተቀዳጅታለች ፡፡
“ማንም ታሸንፋለች ብሎ የገመተ የለም። የሁሉም ዓይን በደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤሊና ሜየር ላይ ነበር” ትላለች ደራርቱ የዚያን ጊዜ የነበረውን ስታስታውስ።
ከኤሊና ቀጥሎ የአሜሪካ እና አየርላንድ አትሌቶች ለማሸነፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ሯጮች ነበሩ። ደራርቱን ያስተዋላትም ያስታወሳትም አልነበረም።
ነገር ግን ሳይታሰብ አፈትልካ በመውጣት ለሃገሯ አልፎም ለአፍሪካ በሴቶች በረጅም ርቀት ቀዳሚና ብቸኛውን ወርቅ አመጣች፤ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ ያመጣች የመጀመሪያዋ ሴት ጥቁር አፍሪካዊት ለመሆንም በቃች።
“የባርሴሎና ኦሊምፒክ የሕይወቴን አቅጣጫ የቀየረ ነበር። ከአስር አለቃነት ወደ ሻለቃነት ደረጃ አደግኩኝ፤ ደሞዜ ከ200 ብር ወደ 600 ብር አደገ፤ ዝናየም ናኘ” ስትል ድሉ ያመጣላትን በረከት ትናገራለች። ወርቅ ሜዳሊያው የእርሷና የሃገሯ ብቻ ሳይሆን የመላ ጥቁር ህዝቦች ድልም ነበር።
ከደራርቱ ድል በኋላም በእርሷ አሸናፊነት መንፈስ የተቃኙ በርካታ ሴት ኢትዮጵያዊያን ሯጮች መታየት ጀመሩ።
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
 
Similar Posts
Latest Posts from