ይህ እለት እሁድ ህዳር 06/2013 ዓ.ም. በሞስኮ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1980 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሃምሌ 12-27/1972 ዓ.ም. በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሞስኮ ከተማ ለ22ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 25 ወንድ እና 2 ሴት አትሌቶች በመም (ትራክ) ከአጭር እስከ ረጅም ርቀቶች፣ በማራቶን፣ በሜዳ ተግባር በውርወራ፣ ዝላይ እና እርምጃ ውድድሮች ለመሳተፍ ተመርጠው በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት ንጉሴ ሮባ እና በረዳቶቻቸው ውሂብ፣ ፅጌ፣ ባሻ ኃይሌ እና ሚስተር ሩዲገን አማካይነት ዝግጅታቸውን በሰንዳፋ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ውስጥ አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል፡፡
የሞስኮ ኦሎምፒክ በአንድ አትሌት በ2 የውድድር ተግባራት 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ የተመዘገበበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ማርሽ ቀያሪው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ5,000 እና 10,000 ሜትር ያስመዘገበው 2 የወርቅ ሜዳልያ ሁሌም በታሪክ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞስኮ ኦሎምፒክ 2 ሴት አትሌቶችን ፋንታዬ ሲራክ እና አምሳለ ወ/ገብርኤል ያሳተፈችና ከዚህ ቀደም ከተሳተፈችባቸው ሁሉ የተሻለ ሜዳልያ ያስመዘገበችበት ወቅት ነበር፡፡
በሞስኮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ5,000ሜ እና 10,000 ሜትር በሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሁለት የወርቅ፣ በመሃመድ ከድር በ10,000 ሜትር እና በሻምበል እሸቱ ቱራ በ3,000 ሜትር መሰናክል በተገኙ 2 የነሃስ፣ በድምሩ በ4 ሜዳልያዎች በኦሎምፒኩ ላይ ከተሳተፉ የዓለም ሃገራት በአትሌቲክስ 6ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
የማርሽ ቀያሪው የሞስኮ ገድል
‹‹ማርሽ ቀያሪው›› በሚለው ቅፅል ስሙ ይታወቃል። በሩጫ ውድድሮች የማብቂያ ዙሮች ላይ ፍጥነቱንና የአሯሯጥ ዘዴውን በድንገት በመቀየር ተፎካካሪዎቹን አስከትሎ የሚገባ ታላቅ አትሌት ነው። ሁሌም ለሀገሩ ያለውን ጥልቅ ስሜትና ፍቅር የሚናገረው ምሩፅ ይህንንም በተግባር አስመስክሯል። በጠንካራ ስራና በጥልቅ የሃገር ፍቅር ስሜት የታጀቡ የበርካታ አንጸባራቂ ድሎች ባለቤት፣ ለፈተናዎች ባለመበገር በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ድርብ ድል የበቃ የጽናት ተምሳሌት … ሻምበል አትሌት ምሩፅ ይፍጠር!
ሶቭየት ኅብረት ያስተናገደችው የ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ መላው ዓለም የምሩፅን ኃያልነት የተመለከተበት ውድድር ነበር። በሙኒክና በሞንትሪያል ኦሊምፒኮች ድልን የማጣጣም ህልሙ የተጨናገፈበት ምሩፅ፤ እንደተለመደው ኢትዮጵያን በ5 ሺ እና በ10 ሺ ሜትር ውድድሮች ወክሎ ቀረበ።
በሙኒክና በሞንትሪያል ኦሊምፒኮች ባለድል የነበረውና 3ኛ የኦሊምፒክ ድሉን ለማጣጣም የተዘጋጀው ፊንላንዳዊው አትሌት ላሲ ቪረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ በመተማመን ተናገረ። የፖርቶሪኮ ግማሽ ማራቶንን በድጋሚ ያሸነፈው ምሩፅ በበኩሉ ‹‹ … ሃሩርም ይሁን በረዶ እኔን ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም … የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ ስለሆነ በፖርቶሪኮው ድሌ አልኮራም …›› በማለት በልበ ሙሉነት ተናገረ።
የውድድሩ ቀን ደረሰና ፍልሚያው ተጀመረ። በ5 ሺ ሜትር ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀረው በ10 ሺ ሜትር ደግሞ 300 ሜትር ሲቀረው ምሩፅ ማርሽ ቀይሮ ተፈተለከ። ምሩፅ ሙኒክ ላይ ያሸነፈውን፣ ሞንትሪያል ላይ እርሱ በሌለበት ባለድል የሆነውንና ‹‹የሞስኮ አየር ጥሩ ከሆነ አሸንፋለሁ›› ብሎ ተናግሮ የነበረውን ፊንላንዳዊውን ላሲ ቪረንን በመርታት በሞስኮ ኦሊምፒክ በ5 ሺ እና በ10 ሺ ሜትር ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፎ ድርብ የኦሊምፒክ ድል አስመዘገበ።
በወቅቱ የ5 ሺ ሜትር ውድድር 2፤ የ10 ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ አንድ ማጣሪያዎች ነበሯቸው። ምሩፅ በ2 የፍፃሜ ውድድሮች አሸንፎ ድርብ ድል ያስመዘገበው ሁሉንም የማጣሪያ ውድድሮች በድል በመወጣት ነበር። በዚህም ምሩፅ በአጠቃላይ የሮጠው 35 ሺ ሜትር ነበር። ይህ ክስተትም የምሩፅን የኦሊምፒክ ድል ልዩና አስደናቂ አድርጎታል። ምሩፅ በአንድ ኦሊምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን በታሪክ መዝገብ ስሙን በደማቁ ማፃፍ ችሏል።
ምሩፅ ስለ ሞስኮ ድሉ በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ‹‹ … አምስት ዙር እንደቀረው የተቀናቃኞቼን እንቅስቃሴና ትርታ ማዳመጥ ጀመርሁ፤ ውጥረት የሚሰፍነው ደወሉ ሲደወል በመሆኑና አቅማቸውን አሰባስበው ከመነሳታቸው በፊት 300 ሜትር ሲቀር ማምለጥ እንዳለብኝ ወሰንሁ፤ ድሉንም ጨበጥኩ›› ብሏል።
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሃምሌ 22/2012
የሞስኮ ልዩ ትዝታ፡-
ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በ10000 ሜትር ውድድር አራተኛ ደረጃን ያገኘ ሲሆን ሆኖም ግን ሁለተኛ የወጣው ካራሎ ማኒንካ (ፊንላናዳዊ) በዶፒንግ ቅሌት የተጠረጠረ ቢሆንም ይህን በወቅቱ የሚከራከር ባለመኖሩ የነሀስ ሜዳልያ
ማግኘት አልቻለም መሀመድ ከድርም የብር ሜዳልያ አምልጦታል፡፡
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
Similar Posts
Latest Posts from