ይህ እለት አርብ ህዳር 04/2013 ዓ.ም. በሜክሲኮ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1968 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከጥቅምት 02-17/1961 ዓ.ም. በሜክሲኮ ከተማ ለ19ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘጠንኝ ወንድ አትሌቶች በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀቶች እና በማራቶን የውድድር ተግባራት ለመሳተፍ ተመርጠው በወቅቱ አሰልጣኝ በነበሩት በስውዲናዊው ሜጀር ኦኒ ኒስካን እና በረዳት አሰልጣኛቸው ንጉሴ ሮባ አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድር ስፍራዉ ተጉዘዋል፡፡
በሜክሲኮ በተካሄደው ኦሊምፒክ የሁለት ተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶን ጀግናው አበበ ቢቂላ በእግሩ ላይ አጋጥሞት በነበረ ህመም ሳቢያ ውድድሩን ማጠናቀቅ ባይችልም የሃገሩ ልጅ ማሞ ወልዴ ለተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ የማራቶንን ድል ከኢትዮጵያ አላስነጠቀም ነበረ፡፡ ማሞ በዚህ ኦሎምፒክ በሶስት የውድድር ተግባራት ተካፍሎ በማራቶን አንድ የወርቅ፣ በ10000 ሜትር አንድ የብር ሜዳልያ እና በ5000 ሜትር የተሳትፎ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በ1968 የሜክሲኮ የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሻምበል ማሞ ወልዴ በማራቶን ወርቅና በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያዎች በማግኘት በኦሎምፒኩ ከተሳተፉ የዓለም ሃገራት 10ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ በዚሁ የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ወቅት የዶፒንግ
ፍተሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደርጓል፡፡
ሜክሲኮና ሻምበል ማሞ ወልዴ
እ.ኤ.አ. በ1968 19ኛው ኦሎምፒያድ በሜክሲኮ ሲካሄድ ከአበበ ቢቂላ በኋላ ለሜዳልያ ውጤት የኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ ከፍተኛ ልምድ የነበረው ምርጥ በወቅቱ የመቶ አለቃ ማዕረግ የነበረው ማሞ ወልዴ ነበር፡፡ እንደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሁሉ ሜክሲኮ ላይ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የተያዘው በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን እንዲወዳደር ነው፡፡ ውጤታማ እንደሚሆንበት ከታመነው የማራቶን ውድድር አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በመጀመርያ በ10ሺ ሜትር ተወዳደረ፡፡ ኬንያዊው ናፍታሌ ቴሞ በአጨራረስ ብልጠት አሸንፎ የወርቅ ሜዳልያውን ሲወስድ ማሞ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የቱኒዚያው መሃመድ ጋሃሚ በሶስተኛ ደረጃ ውድድራቸውን በመጨረስ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡
ማሞ ወልዴ በሶስተኛ የኦሎምፒክ ተሳትፎው የመጀመርያውን የ10ሺ ሜ የብር ሜዳልያ ለመጎናፀፍ የበቃው በ29፡27.75 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በመሸፈን ሲሆን ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሩጫ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይኖራል፡፡
ማሞ በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያውን ከተጎናፀፈበት ድል በኋላ ግን ከአድካሚው ውድድር እፎይ የሚልበት ጊዜ አልነበረውም፡፡ ከሳምንት በኋላ በማራቶን ሲወዳደር የአበበን የድል ታሪክ መድገም እንደሚኖርበትና የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነት የሱ መሆኑን በወቅቱ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ አሳስበውታል፡፡ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር ላይ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ የተደነቀውን አበበ ቢቂላን ለመፎካከር ከተሰለፉት የ44 አገራት አትሌቶች ውስጥ አንዱ ማሞ ነው፡፡
ከ34 ዓመታት በኋላ በታዋቂው የአትሌቲክስ መፅሄት ራነርስ ዎርልድ ላይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የቅርብ ተቀናቃኙ የነበረው አሜሪካዊው ኬኒ ሞር ማሞ ወልዴን በዘከረበት የታሪክ ማስታወሻው በሜክሲኮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ የነበረው የአሯሯጥ ሁኔታ የፃፈው እንዲህ ነበር፡፡
አበበ ቢቂላ ከግራ ጉልበቱ ከፍ ብሎ በሚገኝ ጡንቻው ላይ ፋሻ አስሮ እየሮጠ ነበር፡፡ 10 ማይሎችን ሮጦ ዞር ብሎ ሌላውን የሃገሩን ልጅ ማሞን ይፈልገው ጀመር፡፡ በማራቶን ውድድሩ መላው ዓለም የአሸናፊነቱን ከፍተኛ ግምት የሰጠው ለሻምበል አበበ ቢቂላ እንጅ ለማሞ ወልዴ አልነበረም፡፡ እንደውም ከማሞ ይልቅ አበበን እንደሚፎካከሩ የተጠበቁት የኬንያዎቹ ናፍታሌ ቴሞ፤ ኪፕ ኬኖና አሞስ ቢውት ነበሩ፤ በማለት የኬኒ ሞር የታሪክ ማስታወሻ ይጠቅሳል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መወሳት ያለበት የአበበ ቢቂላ እና የማሞ ወልዴ አሰልጣኝ የነበሩት ኦኒ ኒስካነን ውድድሩን ያስታወሱበት አስተያየት ነው፡፡ ስዊድናዊው አሰልጣኝ ‹‹My Uncle from Africa›› በሚለው መፅሃፋቸው ባሰፈሩት የታሪክ ማስታወሻ ‹‹በማራቶን ውድድሩ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት ሶስቱ አትሌቶች አበበ፤ ማሞ እና መርዓዊ ገብሩ ነበሩ፤ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ በጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ማሞ ነው፡፡ ሶስቱም ኢትዮጵያውያን አጀማመራቸው ጥሩ ነበር፡፡ አበበ ከ5 ኪሎ ሜትሮች በኋላ በመሪዎቹ ተርታ ከነበሩት የሌሎች አገራት አትሌቶች ጋር ሲገሰግስ ነበር፡፡ ማሞ እና መርዓዊ ደግሞ በቅርብ ርቀት እየተከተሉ ናቸው፤ 10 ኪሎ ሜትሮች ሲያልፉ አሁንም አበበ ከመሪዎቹ ጋር መሮጡን ቀጥሏል የተወሰኑ ርቀቶችን እንደተጓዙ ግን የኬንያው ናፍታሌ ቴሞ አበበን ቀድሞት አለፈ፤ … አበበም ከነበረበት ጉዳት ጋር ተደማምሮ ፍጥነቱ እየቀነሰ መጣ….›› በማለት ትዝታቸውን አስፍረውታል፡፡
ሜክሲኮ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን እንደሚያሸንፍ የተጠበቀው አበበ ቢቂላ በህመም ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪዎች ልብ በሃዘን ተሰበረ፡፡ አበበ 16ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ውድድሩን አቋርጦ ከመውጣቱ በፊት ከማሞ ጋር በሩጫ ላይ ያደረጉትን ምክክር አሜሪካዊው ኬኒ ሞር ለራነረስ ዎርልድ በፃፈው መጣጥፍ ላይ ውድድሩን ማሸነፍ እንዳለበት የአደራ ቃሉን ሰጥቶት አበበ ቢቂላ በመጨረሻ ሩጫውን አቋረጠ፡፡
ማሞ ግን ከአበበ ጋር ካደረጉት ምልልስ በኋላ በከፍተኛ ሞራል መሮጡን ቀጠለ፡፡ ዱካውን በመከተል ተፎካካሪ የሆነው የኬንያው ናፍታሊ ቴሞ ነበር፤ የመጨረሻዎቹን የማራቶን ርቀቶችን ለመጨረስ ከሜክሲኮው ኦሎምፒክ ስታድዬም አካባቢ ሲደርሱ ማሞ ፍጥነቱን ጨምሮ አፈተለከና የአሸናፊነቱን ሪባን በጠሰ፡፡ በኦሎምፒክ ማራቶን ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን፣ ለራሱ ደግሞ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ አጠለቀ፡፡ በውድድሩ የመጨረሻ መስመር ላይ ከሁሉም ቀድሞ በመገኘት ድሉን ያደነቀለት አበበ ቢቂላ ሲሆን ከጫነው የአምቡላስ መኪና ወርዶ በድሉ መደሰቱን የገለፀለት ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ነበር፡፡
በሜክሲኮ ኦሎምፒክ የ36 ዓመቱ ማሞ ወልዴ ልዩ ብቃት ለማሳየት የበቃው ውድድሩ ከአዲስ አበባ ጋር በሚመሳሰል ከፍተኛ አልቲትዩድ ላይ በመደረጉ ነበር፡፡ ማሞ በሜልበርን፣ ከዚያም በኋላ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የነበሩት ልምዶችም ቀላል አልነበሩም። ከሻምበል አበበ ቢቂላ ጋር በልምምድ፤ በውድድር እንዲሁም በውትድርና ሙያቸው በነበራቸው ቅርበትም ብዙ የአሯሯጥ ታክቲኮችና ምክሮችንም እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ማሞ ወልዴ በአንደኛነት የኦሎምፒክ ማራቶኑን አሸንፎ የወርቅ ሜዳልያ ሲወስድ ርቀቱን የሸፈነው በ2:20፡26.4 በሆነ ሰዓት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የተከተለውን ናፍታሌ ቴሞ በ3 ደቂቃ ልዩነት ቀድሞ መግባቱ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛው የማራቶን አሸናፊ ያስመዘገበው የሰዓት ልዩነት ነበር፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ ግንቦት 19/2010 ዓ.ም. እለቱን በጋራ እንዘክረው፤

 

 

Similar Posts
Latest Posts from