ይህ እለት ሃሙስ ህዳር 3/2013 ዓ.ም. በቶኪዮ ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1964 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 14 1957 ዓ.ም. በጃፓኗ-ቶኪዮ ከተማ ለ18ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ አምስት ወንድ አትሌቶች በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀቶችና በማራቶን የውድድር ተግባራት ለመሳተፍ ተመርጠው በወቅቱ አሰልጣኝ በነበሩት በስውዲናዊው ሜጀር ኦኒ ኒስካን እና በረዳት አሰልጣኛቸው ንጉሴ ሮባ አማካይነት ዝግጅታቸውን በደብረ ዘይት አየር ኃይል ካምፕ አከናውነው ወደ ውድድር ስፍራዉ ተጉዘዋል፡፡
የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ለሮም የማራቶን ጀግና ሻምበል አበበ ቢቂላ በድጋሚ በማራቶን የኦሎምፒክን ሪከርድ በማሻሻል ጭምር ድል ሲያደርግ ድፍን የጥቁር ህዝቦችን በኩራት ቀና ያደረገበት ኦሊምፒክ በመሆኑ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ እንዲሁም የውድድሩ አስተናጋጅ ከተማ ቶኪዮ ሲዘክሩት ይኖራሉ፡፡
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በማራቶን በሻምበል አበበ ቢቂላ በተገኘ አንድ የወርቅ ሜዳልያ በኦሊምፒኩ ላይ ከተሳተፉ የዓለም ሃገራት በአትሌቲክስ 10ኛ ደረጃ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
ቶኪዮና ሻምበል አበበ ቢቂላ
የ1957 ዓ.ም 18ኛው የቶክዮ ኦሊምፒክ ሊካሄድ አርባ ቀናት ሲቀረው አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር ልምምድ ላይ ነበር። በልምምዱ ላይ እያለም ህመም ቢሰማውም ህመሙን ችላ በማለት ልምምዱን ቀጠለ። ነገር ግን በልምምድ ላይ ራሱን ስቶ ወደቀና አንስተው ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱት ህመሙ የትርፍ አንጀት መቁሰልሆኖ ተገኘ። ወዲያው ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ለጥቂት ቀኖች ካገገመ በኋላ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ በምሽት ልምምዱን ቀስ በቀስ ቀጠለ።
አበበ ቢቂላ ከኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ጋር አብሮ ወደ ቶኪዮ ሲጓዝ በርትቶ ይወዳደራል ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም። አበበ ግን ጫማ አድርጎ ለዚህ ማራቶን ውድድር ጥቅምት 11 ቀን ከአርባ አንድ አገሮች ከተውጣጡ ሰባ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ጋር ተሰለፈ።
ለአበበ ቢቂላ ምንም አዲስ ዘዴ አላስፈለገውም። አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን እንደ ሮማው ኦሎምፒክ ከፊት ከሚመሩት ቡድኖች ጋር እስከ ሃያ ኪሎ ሜትር ድረስ አብሮ እንዲሮጥና ከዚያ በኋላ ውድድሩን እንዲመራ መከሩት። በዚህም ዕቅድ መሠረት ሩጫውን ጀምሮ ፍጥነቱን በጥንቃቄ ቀስ በቀስ እየጨመረ ሄደ። በአሥራ አምስተኛው ኪሎ ሜትር ላይ አብረውት የነበሩት የአውስትራሊያው ሮን ክላርክ እና የአየርላንድ ጄምስ ሆጋን ብቻ ነበሩ። አበበ ቢቂላ በቀዶ ጥገናውም ሆነ በሞቃታማው የአየር ሁኔታ ምንም ዓይነት ችግር አልታየበተም። እንዲያውም ሲሮጥ ለሚመለከተው ከመሬት በላይ የሚንሳፈፍ ይመስል ነበር። አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን ትንሽ ጉልበት በመጠቀም እንዴት መሮጥ እንዳለበት ያስተማሩትን አበበ ቢቂላ በተግባር ላይ ሲያውለው እና ሩጫው ምንም ዓይነት ጥረት የማያስፈልገው ያስመስለው ነበር።
አበበ ቢቂላ ኦሎምፒክ ስታዲዮሙ ውስጥ የገባው ብቻውን ነበር። በዚያም ይጠባበቅ የነበረው ሰባ ሺህ ተመልካች በከፍተኛ ሁኔታ አድናቆቱን ገልጾለታል። በዚህ ውድድር ላይ የራሱን ክብረ ወሰን በድጋሚ በመስበር አሻሽሎታል። አዲሱ ክብረ ወሰንም 2፡12፡11.2 ሰዓት ነበር። ውድድሩንም እንደጨረስ ምንም አይነት ድካም አልታየበትም። እንዲያውም ገና ሊሮጥ የሚሰናዳ ነበር የሚመስለው። ተመልካቹን በጣም ያስገረመው በውድድሩ ምክንያት ጡንቻው እና መገጣጠሚያዎቹ እንዳይተሳሰሩ የተለያዩ የሰውነት ማቀዝቀቀዣ ስፖርቶች ሲሰራ መመልከታቸውና በተጨማሪም ያሳይ የነበረው እርጋታ እና ቅልጥፍና ነበር። አበበ ከውድድሩ በኋላ ተጠይቆ ሲመልስ ሌላ አስር ኪሎ ሜትር ጨምሮ መሮጥ ይችል እንደነበር ተናግሯል። ደምሴ ወልዴ በአሥረኛ ደረጃ ሲጨርስ ማሞ ወልዴ ግን አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ላይ አቋርጦ ከውድድሩ ወጥቷል።
አበበ ከሮም ድል አራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ ድሉን ሲደግም የኦሊምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ድል ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጸመ። ይኸ ብቻ አይደለም ባሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይ በ2፡13፡55 ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1፡43.8 የሰበረበት ነው::
ቻርሊ ሎቬት “ማራቶን በኦሎምፒክ” በሚለው መጽሐፉ ላይ ስለቶክዮው ውድድር ሲዘግብ “ግማሽ ሩጫውን እንዳገባደደ በአምስት ሰከንድ ልዩነት ይመራ ነበር” ይላል ። ሎቬት “የክፍለ ዘመኑ ሩጫ ብዙ ታሪክ የተጻፈለት እና የተወራለት ውድድር ነው” ሲል አበበ ቢቂላን ደግሞ “ወደር የማይገኝለት እውነተኛ የማራቶን ሯጭ ምሳሌ ነው” ይለዋል። ሪቻርድ በኔዮ ደግሞ “የማራቶን ጌቶች” በሚለው መጽሐፉ “አበበ ቢቂላ ሩጫው ምንም አይነት ጥረት የማያስፈልገው ያስመስለዋል” ብሎታል። “አበበ ቢቂላን ሲያዩት ረጅም ቀጠን ያለ በቀላሉ ተሰባሪ ይመስላል፣ ነገር ግን ከሚገባው በላይ ጠንካራ አትሌት” ነው ይልና “አበበ ቢቂላ ማናቸውም የማራቶን ሩጫ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚገባው ምሳሌ ነው” ብሏል። ቀጥሎም “አበበ ቢቂላ ተፈጥሮ ካፈራቻቸው ምርጥ የዓለማችን አትሌቶች አንዱ ነው” ይልና “በዚህም (የቶክዮው) ድል ተጨምሮ ለሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን ያሸነፈ ብቸኛ አትሌት አድርጎታል” ይላል።
አበበ ቢቂላ ሁለተኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሰ የአዲስ አበባ ሕዝብ ተገልብጦ ወጥቶ የጀግና አቀባበል ካደረገለት በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ የሻምበልነት ማዕረግና አዲስ ቮልስ ዋገን ቢትል ሸለሙት።
እለቱን በጋራ እንዘክረው፤
    
 
Similar Posts
Latest Posts from