ይህ እለት ረቡዕ ህዳር 2/2013 ዓ.ም. በሮም ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1960 በአትሌቲክስ ተሳትፎና ድል ኢትዮጵያን ከአለም ጋር ያስተዋወቁ የአትሌቲክስ ጀግኖች ቀን ነው፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከነሀሴ 12-26/1952 ዓ.ም. በጣሊያኗ – ሮም ከተማ ለ17ኛ ጊዜ በተካሄደው የበጋ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ሰባት ወንድ አትሌቶች በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀቶችና በማራቶን የውድድር ተግባራት ለመሳተፍ የተመረጡት አትሌቶች በደብረዘይት አየር ኃይል ካምፕ ውስጥ በወቅቱ አሰልጣኝ በነበሩት በስውዲናዊው ሜጀር ኦኒ ኒስካን እና በረዳት አሰልጣኛቸው ንጉሴ ሮባ አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድር ስፍራዉ ተጉዘዋል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ ስትካፈል በባዶ እግሩ በሮም አደባባይ በማራቶን ውድድር ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአህጉረ አፍሪካ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ጭምር በመስበር ባስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ ስሙን በወርቅ የፃፈበት በመሆኑ ሁሌም ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፡፡
በሮም ኦሎምፒክ በማራቶን በተገኘ አንድ የወርቅ ሜዳልያ በኦሎምፒኩ ላይ ከተሳተፉ የዓለም ሃገራት በአትሌቲክስ 10ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለናል፡፡
ሮምና ሻምበል አበበ ቢቂላ
አገራችንን ወክለው በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከአሰልጣኙ ጋር ወደ ሮም ካመሩት ተወዳዳሪዎች መሃል ለማራቶን ሩጫ የተመረጡት አበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ነበሩ። ውድድሩ አንድ ወር ሲቀረው ሮም ከተማ ውስጥ ሲሰለጥኑ የቆዩት ሁለቱ አበበዎች፣ የሩጫውን መንገድ በጥንቃቄ እንዳጠኑና ሲሮጡ በባዶ እግርም በጫማም እንደተለማመዱ፣ አበበ በጫማ ሲሮጥ በአምስትና በስድስት እርምጃዎች ስለሚዘገይ እንዲሁም አዲሱ ጫማ ልጦት እግሩ ውሃ በመቋጠሩ በባዶ እግሩ መሮጥ የግድ ሆነበት ስለሆነም ሁለቱም በባዶ እግራቸው እንዲሮጡ መወሰኑን አሰልጣኙ ኒስካነን ከውድድሩ በኋላ (Duvbo IK’s Annual Magazine 1960:) ለተባለ መጽሔት የተናገሩት ያሳያል። ኦኒ ኒስካነን ሩጫው በማታ ሰዓት ስለሚካሄድ የሞቀው የመንገድ ሬንጅ እንደማይጎዳቸውና ከውሳኔውም በኋላ ውስጥ እግራቸው እንዲጠነክርም ኦሊምፒክ መንደሩ ውስጥ ሁሉ በባዶ እግራቸው እንደነበር ይሄዱ እንደነበር ይነግሩናል። አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን ሁለቱን የሃገራችን ሯጮች የጊዜውን ምርጥ ማራቶን ተወዳዳሪዎች የነበሩት የሞሮኮው ራህዲ ቤን አብዴሰላም፣ የኒውዚላንድ ባሪ ማጊ፣ የሶቪዬቱ ኮንስታንቲን ቮሮብዮቭ እና በወቅቱ የማራቶን ክብረ ወስን ባለቤት የነበረው ሰርጌይ ፖፖቭ እና የብሪታንያ ተወላጅ ዴኒስ ኦጎርማን እንደሆኑ በጥብቅ አስጠንተዋቸዋል። ራህዲ ይለብሳል የተባለው የመለያ ቁጥሩ 26 መሆኑን ያጠናው አበበ ውድድሩ ላይ ይሄንኑ ቁጥር ለመለየት ሲፈልገው ለካስ ራህዲ በ10,000 ሜትር ውድድር ላይ ለብሶት የነበረውን መለያ ለብሶ ኖሮ አጠገቡ ሲሮጥም አላወቀውም።
አበበ በውድድሩ ወቅት ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎ ሜትር በነበረው ፍጥነት አብዛኛዎቹን ባላጋራዎቹን ጥሎ ሲሄድ የቀረው ራህዲ ብቻ ነበር። እሱም ብዙ አብሮት አልቆየም። አበበ ድሉን ከተቀዳጀ በኋላ “ከተማው ክልል ውስጥ ስገባ ከኋላዬ የምሰማቸው ኮቴዎች እየቀነሱ መጡ። ፍጥነትም ስጨምር እስከነ አካቴው ድምጽም አልነበረም። ለአንድ ሰዓት ሙሉ የኮቴዎችን ድምጽ ሳዳምጥ ከቆየሁ በኋላ አሁን ጸጥታ ሲሰፍን የተከተለኝ እንዳለ ለማየት ፊቴን ማዞር አስፈላጊ አልነበረም” ብሏል። አበበ አስተሳሰቡ ተፎካካሪ እስከሚያጋጥመው ድረስ ጉልበቱን ለመቆጠብ ስለነበር በዚህ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ክብረ ወሰኑን በተሻሻለ ውጤት ይሰብር እንደነበር ኒስካኒን ጥርጣሬ እንዳልነበራቸውም ገልጸዋል። ሆኖም አበበ ቢቂላ ውድድሩን 2:15:16.2 ሰዓት በማገባደድ የዓለምን ክብረ ወስን ሰብሮ ወርቅ አገኘ። ራህዲ ሁለተኛ እና ባሪ ማጊ ሦስተኛ ወጡ።
የጣልያን ጋዜጦች በነጋታው “ኢትዮጵያን ለመውረር የጣሊያን አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው” የሚል ጽሁፍ ይዘው ወጥተው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ለብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።
የአበበ ቢቂላ አዲሱ የዓለም ክብረ ወሰን = 2:15:16.2
የሰርጌይ ፖፖቭ አሮጌው የዓለም ክብረ ወሰን = 2:15:17.0
Similar Posts
Latest Posts from