ማክሰኞ ሐምሌ 28/2012 ዓ. ም. ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ለስፖርት ሚድያ አካላት በኢአፌ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
የፌዴሬሽኑ ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ፣ የውድድርና ተሳትፎ ሥራ ሂደት መሪው አቶ አስፋው ዳኜ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን በየተራ ማብራሪዎችን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በክልልና ከተማ አስተዳደሮች ሥር ለሚገኙና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና አንጋፋ አትሌቶች የገንዘብ ድጋፍ፣ እንዲሁም ለቀጣይ ሃገራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚያደርገው አጠቃላይ ዝግጅት ማሳያቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፡-
 ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ጀምሮ በአትሌቲክሱ ውስጥ ለሚገኙ የብሔራዊ አትሌቶችና አሰልጣኞች ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመስራት፣
 እነዚሁ አትሌቶችና አሰልጣኞች በወረርሽኙ ሳቢያ ወደየቤታቸው በሚመለሱበት ወቅት ደግሞ በገንዘብ፣ በስፖርት አልባሳትና በስልጠና ትጥቆች ድጋፍ በማድረግ የአትሌቶችና አሰልጣኞች ሞራል ተገንብቶ እንዲቆይ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ካለው የውስጥ ገቢ በመቀናነስ አትሌቶችና አሰልጣኞች፣ እንዲሁም አንጋፋ አትሌቶችን በዚህ ሁኔታ ሲደግፍ ቢቆይም ወረርሽኙ አሁንም ባለመገታቱና በተለይ በክልሎቻና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ድጋፍ የሚሹ ነገ አገርን በመወከል በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን በድል ማስጠራት የሚችሉና ተስፋ የሆኑ አትሌቶች ደግሞ ወረርሽኙ በፈጠረው ምስቅልቅሎሽ ተጠቂ እንዳይሆኑ ለማገዝ ሐምሌ 22/2012 ዓ. ም. የፌዴሬሽናችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ ወደ 3.1 ሚልዮን ብር በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ አትሌቶችና አሰልጣኞች፣ እንዲሁም 300 ሺህ ብር የሚሆን ገንዘብ ደግሞ በአዲስ አበባ አካባቢ ለሚኖሩና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 100 ለሚሆኑ አንጋፋ አትሌቶች (ከዚህ ውስጥ 150 ሺህ ብሩ በአቶ አብነት ገ/መስቀል የሚሸፈን ነው)፣ በአጠቃላይ በድምሩ 3 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ መድቦ መጨረሻ ላይ በሚገለጹት መስፈርቶች መሠረት የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች እንዲሁም በዚያው ከሚገኙ የስፖርት ኮሚሽኖቻቸው ጋር በመሆን የራሳቸውን አስተዋጽኦ አክለውበት ድጋፉን እንዲሰጡ ለማድረግ ታስቦ የተወሰነ ውሳኔ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተጓዳኝ የሚታየው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከአህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮች ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽናችን እያደረገ ያለው ዝግጅት ነው፡፡
አትሌቶቻችን በወረርሽኙ ምክንያት ወደየቤታቸው ሲመለሱ በምን አይነት መንገድ ከአሰልጣኞቻቸውና ከፌዴሬሽናቸው ጋር በመገናኘት ሊከተሉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄና የልምምድ ሁኔታ ምክር የተሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በ‹‹ሜይንቴናንስ›› ስልጠና አቅማቸውንና ጤንነታቸውን እየጠበቁ ለየትኛውም አህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባር 3 የቴሌቪዥንና የተለያዩ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎችን፣ የፌዴሬሽኑን ማህበራዊ ሚዲያዎችና የአሰልጣኞች ሞባይል ስልኮችን በመጠቀም ሥራው እየተሰራ ይገኛል፡፡
የመምረጫ መስፈርት
1. በክልልና ከተማ አስተዳደሩ ክለቦች የፈረሱባቸው ወይም ክለቡ ደመወዝ ያቋረጠባቸው አትሌቶች፤
2. በክልልና ከተማ አስተዳደሮች በተቋቋሙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚገኙ አትሌቶች፤
3. በክልልና ከ/አስተዳደር የሚገኙ የኘሮጄክት አትሌቶች እና አሠልጣኞች፤
4. በአዲስ አበባ ከ/አስተዳደር ከማናጀሮች ጋር በመጠጋት በግል ስልጠና የሚያገኙና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ አትሌቶች ናቸዉ፡፡
ማሳሰቢያ፡-
 በ2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ያገኙ የብሔራዊ ቡድን እና የኦሎምፒክ አትሌቶችና አሰልጣኞችን አያካትትም፡፡
የኮቪድ -19 የማገገሚያ ስልት እና ማስፈፀሚያ
1. የዕቅዱ አስፈላጊነት፡-
 ኮሮና ቫይረስ በሀገራችን አትሌቶች እና የአትሌት ማህበረሰብ ላይ ያደረሰውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ደረጃ በደረጃ በዘላቂነት መፍታት በማስፈለጉ ፣
 የአትሌቶችና የአትሌት ማህበረሰብን ለበሽታው ተጋላጭነታቸውን መቀነስ በማስፈለጉ ፣
3. የዕቅዱ ዓላማ፡-
• የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ–19) በሀገራችን በአትሌቲክስ ማህበረሰብ ላይ ያደረሰውን ዘርፈ-ብዙ ጉዳት በጥናት በማስደገፍ፣ ተጐጂዎችን፣ የጉዳቱን ደረጃ፣ የተጐጂዎችን መጠንና ጥልቀት በመለየትና በመተንተን ሁለንተናዊና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር፣
ግቦች
• ወረርሽኙ በአትሌቲክስ ማህበረሰብ ላይ ያደረሰውን የጉዳት መጠን ፤ጥልቀት በተለይ በአዲስ አበባ አካባቢ ለመለየት ፈጣን የዳሰሳ ጥናት ተከናውኗል ፣
• የአትሌቱን ማህበረሰብ ለማገዝ የሚያስችሉ የጤና፣የስነ-ልቦና፣ የምግብ እና በወረርሽኝ ጊዜ ስለሚደረግ የህይወት ክህሎት ዘይቤ ወዘተ… የግንዛቤ ማዳበሪያ ትምህርታዊ ሰነዶችን ተዘጋጅተው ስልጠና ተሰጥቷል ፣
• በብዙሃን መገናኛ ለአትሌቱ ማህበረሰብ በቋሚነት ወረርሽኙ እስከሚወገድ የሚያገለግል የመከላከልና በየአትሌቲክስ ዲሲፕሊን ላይ ያተኮረ አትሌቱን በጤንነትና ብቃት የማቆየት ፕሮግራም ተዘጋጅተው ስልጠና ተሰጥቷል፣
• ከመንግስት በሚገኘው ፋይናንስ መሰረት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ አትሌቶችና የአትሌት ማህበረሰብ ሊሰጥ የሚገባው የድጋፍ ዓይነት፤መጠን፤ድጋፉ የሚሰጥበት ቦታና ፕሮግራም በተጨማሪም ድጋፉ የሚዘልቅበት ጊዜ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በዝርዘር ተዘጋጅቷል
• በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ውስጥ ያሉትን የአትሌቲክስ ክለቦች/ ስልጠና ማዕከላት፣ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ያለበትን ሁኔታ በጥናት በማስደገፍ ተዘጋጅቷል፣
• በቀጣይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ባለድርሻ አካላት የሚደገፍ ቋሚ የአትሌቶችና የአትሌት ማህበረሰብ የመረዳጃ ፈንድ የሚቋቋምበትን ስልት ተዘጋጅቷል ፣
• የአትሌቱን ማህበረሰብ ችግሮችን ቀድሞ የመዘጋጀት፤ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም ለማጐልበት ከፕሮጀክቶች ጀምሮ ተካታታነት ያለው የህይወት ክህሎት ሥልጠና የሚሰጥበት ስርዐት ተዘርግቷል
• ጠንካረና ቫይረስ መከላከልን እና መቆጣጠርን በአትሌቶች ስልጠና ማሰቀጠል ላይ በሚዘጋጅ የስልጠና ፕሮግራም በጥንቃቄ መተግበር ፤አፈጻጸሞችን መከታታልና ድጋፍ ማድረግ ፤ ወደ ውጪ ጉዞ ከመደረጉ በፊት መሟላት የሚገባቸውን የኮቪድ – 19 ፍተሻዎች ከባድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት መፍጠርና ማከናወን የሚስችል አትሌቶች በግልና በብሔራዊ ደረጃ ለአህጉርና አለም አቀፍ ውድድሮች ጤናማና ብቁ ተሳታፊ የሚሆኑበት ስርዓት ተፈጥሯል፤
እነዚህና ተዛማጅ አትሌቲክሳዊ ጉዳዮች በስፋት ከመዳሰሳቸውም በላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
,,,,,,,,,,,//,,,,,,,,,,,,,
Similar Posts
Latest Posts from