የኢትዮጵያ አትሌቲክስን ስፖርት ለማልማት ከመንግስታዊ ድርጅቶች እስከ የተለያዩ ግለሰቦች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ እንደነበር ይታወቃል። ለዚህም ጥረታቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው 23ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በወሰነው መሠረት ግለሰቦቹ ላበረከቱት የላቀ አበርክቶ የእውቅናና የሽልማት መርሃግብር አካሂዷል። በዚህም የሽልማት መርሃ-ግብር አትሌቶቻችን በሀገር ውስጥ፣ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በአለም አደባባይ ከፍ አድርገው በድል ሲመለሱ በግላቸው ያደርጉ ለነበረው አስተዋጽኦ ምንም እንኳ በህይወት ባይኖሩም አቶ አቤሴሎም ይህደጎን የክብር ተሸላሚ አርጎ የመረጠ ሲሆን ሽልማታቸውንም የድርጅታቸው የገበያና ሽያጭ ሃላፊ ለሆኑት ለአቶ ሮቤል ዘላለም ሰጥቷቸዋል።
በመቀጠልም እነ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን የመሳሰሉ ብርቅዬ አትሌቶችን ለዓለም ያበረከቱትና የአትሌቲክሱ ውጤት ቁልፉ ሰው ለነበሩት አሰልጣኝ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬን በዓለም አትሌቲክሰ ለተሰጠው እውቅና ፌዴሬሽኑም የተሰማው ደስታ በልዩ ሽልማት ሲገልፅ ለበቆጂ ከዓለም አትሌቲክስ በአትሌቶች ምንጭነት ለተሰጣት እውቅና ለበቆጂ አት/ማሰልጠኛ ማዕከል ሽልማት ተበርክቷል።
ጉባኤው የክብር አባላትና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት ለሁለት ተርም ያገለገሉ እንዲሁም ከ20 ዓመታት በላይ በውጤታማነት በአትሌትነት ላሳለፉ አምስት ግለሰቦች ማለትም አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሄር፣ አቶ መአር አሊ፣ ዶ/ር ሳምሶን ባዩ፣ ሻ/ቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እና አትሌት ፋጡማ ሮባን በመመሪያው መሰረት በጉባኤው በክብር አባልነት አሰይሟል
ሽልማቱ ቀጥሎ ፌዴሬሽኑን በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ለበርካታ ዓመታት ላገለገሉትና የዓለም አትሌቲክስ የቬትራን ፒን ተሸላሚ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎን ፌዴሬሽኑ የእንኳን ደስ አልዎት ሸልሟቸዋል። በመቀጠልም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን በመተካት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት እየመራች ያለችውን ፍልቅልቋን አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን በ2019 ከአምስት ዓለም አቀፍ ተቋማት ላገኘችው እውቅና ልዩ ተሸላሚ ያደረገ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑትንና አስተዳደራዊ ስራዎችን በIAAF አሰራር ደረጃ በብቃት በመምራት ለሰባት ዓመታት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የስራ አስፈፃሚው የልዩ ተሸላሚ አድርጓቸዋል ።
ሀገሩን ወክሎ በሁለት ተከታታይ አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወርቅ ላስገኘው አትሌት ሙክታር እድሪስ፣ በ2019 ሪከርድ ለሰበሩ አትሌት ሳሙዔል ተፈራ፣ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻና አትሌት ለተሰንበት ግደይ፣ ለተተኪና ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከውጤታማ አትሌቶቻችን ጀርባ ላሉ አሰልጣኞች ኃይሌ እያሱ፣ ብርሃኑ መኮንን ፣ ለአትሌት ተወካይ ጆስ ኸርመንስ፣ ለአሰልጣኝ ሻ/ል ቶሎሳ ቆቱ ከክለቦች መከላከያ፣ ኦሮ/ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት፣ ኦሮሚያ ውሃ ስራዎች፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ፖሊስ ካላይ እውቅና የተሰጣቸው አትሌቶችን በማፍራት እንዲሁም በ2011 ዓ.ም. ውጤታማ ለነበሩ ስምንት ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች እና ስምንት ክለቦችና ተቋማት እንዳስመዘገቡት ውጤት ከገንዘብ እስከ ቁሳቁስ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ከእለቱ የሽልማት መርሃ-ግብር ሁሉ የላቀና የጉባኤው ድምቀት የነበሩት የሻ/ል ባሻ ዋሚ ቢራቱ ሽልማት ነበር ። በአስገምጋሚ ድምፃቸው ለተደረገላቸው ሽልማት ምስጋና ሲያቀርቡ ታዳሚው በሙሉ በጥንካሬያቸው ይገረም ነበር። እንዲህ አይነት የሃገር ባለውለታዎች መታወስ ያለባቸው በህይወት ሳሉ ነውና የስራ አስፈፃሚው ይህንን በመወሰኑ ሊመሰገን ይገባዋል በሌላ በኩል ክብርት ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠናን በፌዴሬሽኑ በአመራርነት ለነበራቸው ሚናና ውጤት በገንዘብ ተሸልመዋል።
በጉባኤው ማጠቃለያም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ በመዝጊያ ንግግራቸውም “አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መለያዋ በመሆኑ እናንተ የጉባኤው ተሳታፊዎችና የስፖርቱ አመራሮች በማይመቹ አኳኋኖች ውስጥ እንኳ ሁናችሁ ቀን ከሌት ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ስፖርት ኮሚሽንን በመወከል ምስጋና ሳቀርብላችሁ ደስ እያለኝ ነው።” ካሉ በኋላ አክለውም “የማዘውተሪያ ስፍራ ችግርን ለመቅረፍ እንደመንግስትና እንደ ባለድርሻ አካልነታችን ለመንግስት እንደ ጥያቄ የምናቀርበው ጉዳይ ሳይሆን ጥያቄያችሁን ለመፈፀም ቀን ከሌት እንደምንሰራ በጉባኤተኛው ፊት ቃል እገባላችኋለሁ” ሲሉ ንግግራቸውን ሲያጠናቀቁ የኢ.አ.ፌ 23ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ዜናና ምስል ቴዎድሮስ ለገሰ

 

Similar Posts
Latest Posts from