አዲስ አበባ ኅዳር 27/03/2012 በኤልያና ሆቴል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 23ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤውን በኤልያና ሆቴል ሲጀምር ዶ/ር ሂሩት ካሳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በንግግር አስጀምረውታል።

 

 

 

 

 

 

 

በመቀጠል ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኢአፌ ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት የሚከተለውን የመክፍቻ ንግግር እና ሪፖርት አቅርበዋል 

‹‹ በቅድሚያ እንኳን ለ23ኛው የፌዴሬሽናችን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በሰላም አደረሳችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ፡፡ የስፖርት ማህበራትን ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ ቁጥር 6/2011 እና በዓለም አትሌቲክስ ሕገ-ደንብ መሠረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቋቁሞ የሃገራችንን አትሌቲክስ ስፖርት በበላይነት እየመራ በአህጉራዊና በዓለማቀፋዊ የውድድር መድረኮች በመሳተፍ የሃገራችንን በጎ ገጽታ የበለጠ ለመገንባትና ለማስቀጠል ጎላ ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ፌዴሬሽናችን የእለት ተእለት ተግባሩን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ በሃገር ውስጥ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ከልዩ ልዩ የአትሌቲክስ ስፖርት ማህበራት፣ በዋናነት ከክልልና ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችና ስፖርት ቢሮዎች፣ ከስፖርት ክለቦች፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ኢምባሲዎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋማት፣ ከአትሌት ተወካዮች እና ከሀገራት ፌዴሬሽኖች ጋር የተሳለጠ የሥራ ግንኙነት አድርገናል፡፡በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ታቅደው የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ በዝርዝር በጽ/ቤት ኃላፊው የሚቀርብ ሆኖ ጎላ ካሉት መካከል ሥራ የጀመረው የፈረስቤት የስልጠና ማዕከል፣  በጉጂ አዲስ የሚከፈቱ የስልጠና ማዕከላት በመገንባት ላይ ያለው የቲሊሊ የስልጠና ማዕከላት ዕድሉን አግኝተን በአካል ተገኝተን ከጎበኘን በኋላ የተተኪ አትሌቶች ልማት ከማፋጠን አኳያ ደግፎ ቶሎ ወደተግባር እንዲገቡ ለማስቻል የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ አቅጣጫ ተቀምጦ በዕቅድ ውስጥ በማካተት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች የክልልና ከ/አስተዳደር ፌዴሬሽኖች ለመስራት ተነሳሽነት ካላቸው በዚህ መንገድ የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ 

ክቡራትና ክቡራን

 ምንም እንኳን የማዘውተሪያ ስፍራ የሚገነባው በመንግስት ቢሆንም በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን የብሔራዊ አትሌቶች የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ከለገዳዲ ለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም የልምምድ አሸዋ ትራክና ጥርጊያ ሜዳ ግንባታ  ሂደቱን ጠብቆ መፈጸም ስላለበት በዚህው አግባብ ስራው እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተግባር የተባበሩንን አካላት በዚህ አጋጣሚ ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከተከናወኑ ስራዎች አንዱ የአንጋፋ አትሌቶች ማህበር ማቋቋም ሲሆን ከሰነድ ዝግጅት እስከ ፋይናንስ ድጋፍና የአመራርነት ሚናውንም በመወጣት ሃገራችንን በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ መድረክ ስምና ዝናዋን ያስጠሩ በእድሜ ቅብብሎሽ ለተገኙ አትሌቶች አርአያ የሆኑ ብርቅዬ አንጋፋ አትሌቶቻችንን በማህበር በማደራጀት በአንድ ጥላ ስር እንዲሰበሰቡ የተደረገ መሆኑና ራሳቸውም ተጠቅመው ከፍ ዝቅ ለሚለው አትሌቲክስ ውጤታችን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ በር ተከፍቷል፡፡ በምስረታው ጊዜም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 100 ሺ ብር፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮቴሚቴ 200 ሺ ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ በየዓመቱ 100 ሺ ብር እና በየዓመቱ 100 ሺ ብር ለመደፍ ቃል ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ብለው የገቡ የስፖርት ትጥቆችን ለብልሽት ከመዳረጋቸው በፊት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ በመስጠትና አቅጣጫ በማስቀመጥ አትሌቱ ሊጠቀምባቸው የሚችሉትን የመለየት ስራ በመስራት ለአራቱ የሰልጠና ማዕከላት እና 37 ፕሮጄክቶች እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ለስልጠናና ለውድድር ሊያገለግሉ የማይችሉትን ለአንጋፋ አትሌቶች የተላለፈ ሲሆን በድምሩ ብር 888,118 (ስምንት መቶ ሰማኒያ ስምንት ሺ አንድ መቶ አስራ ስምንት ብር) የሚገመት የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ ንብረት የሆነው ብሔራዊ ሆቴል ይጠቀምበት የነበረውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ለስልጠናና ማዕከላት ማለትም ለሀገረ-ሰላም፣ ለማይጨው፣ ለበቆጂና ለደብረ-ብርሃን እንዲገለገሉበት የተላለፈ ሲሆን በሌላ በኩል ሰባት ለሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ቀሪ ቁሳቁሶችን የፋይናንስ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በሽያጭ ለማስተላለፍ እየተሰራ ይገኛል፡፡ 

ክቡራት እና ክቡራን

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ሥራዎች አንዱ የአበረታች ቅመሞች ግንዛቤ በመፍጠር የመከላከል ሥራ መሥራት ሲሆን፡- ለአትሌቶች፣ ለአሰልጣኞችና ለአትሌት ተወካዮች በአበረታች ቅመሞችና ተዛማጅ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ፌደሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው የተመረጡ ውድድሮች፣ በአህጉራዊና በዓለም ዓቀፍ ውድድር ዝግጅት ጊዜ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል፣ ለምርመራም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ እንዲሁም ከውድድር ውጪ ለሚደረጉ ምርመራዎች የአትሌቶች የመገኛ አድራሻ አሞላል ላይ ክትትል እና ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ፌደሬሽኑ ካደረጋቸው ዘርፈ ብዙ የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ ሀገርን ወክለው ለተወዳደሩ አትሌቶች የሰነ-ምግብ እና ቅድመ ጤና ምርመራ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል፡፡

የአትሌቲክሱን ህልውና ጠብቀን ለማስቀጠል በተተኪ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በየደረጃው ለሚገኙ የስፖርት ባለሙያዎች የማሰልጠን ክህሎታቸውን ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ የዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲሁም የሃገር ውስጥ የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ስልጠና ለባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የአትሌቲክስ ስፖርት መጨረሻ የመለካው በውድድር በመሆኑ ለተተኪና ለኤሊት አትሌቶች የውድድር ዕድል ከመፍጠር አኳያና በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪና ውጤታማ የሚያደርጉንን ተተኪ አትሌቶች ለማፍራት 11 የሃገር ውስጥ ውድድሮችን በማዘጋጀት ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ባሳለፍነው በጀት ዓመት ጉልህ አፈፃፀም ከታየባቸው ተግባራት ውስጥ የአህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ውድድር ቀዳሚው ሲሆን በናይጄሪያ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በኮትዲቯር የታዳጊና ወጣቶች የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በሞሮኮ ራባት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በአርጀንቲና የዓለም ታዳጊ ኦሎምፒክና በዴንማርክ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እና በፊንላንድ የአለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ተሳትፎ ያስቀመጥነውን ራዕይአችንን ለማሳካት ችለናል፡፡ የተገኙት ድሎቻችን ህዝባችንና መንግስታችንን ጭምር ደስ ያሰኙ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ለተመዘገበው ውጤት የኢፌዲሪ መንግስት በሃገራችን ፕሬዝደንትና በጠቅላይ ሚኒስትራችን እጅ እውቅናና ሽልማት አግኝተናል፡፡ ፌዴሬሽናችን በበጀት ዓመቱ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶቻችን፣ አሰልጣኞቻችን፣ የህክምናና የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች(በአጠቃላይ የልዑካን ቡድን) እንዲሁም ውጤታማ ለሆኑ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ በየደረጃው ሸልሟል፡፡  ነገር ግን እንደ እንዲህ አይነት ድሎቻችንን አጠናክረንና በተጨማሪ ውጤቶች አጅበን፣ በመደመር መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከሰራን ሃገራችንን በጋራ ልንገነባ ያስችለናል፡፡ ይህንን ተግባራችንን በማስቀጠል በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሃገራችንን ውጤት በተለይም የሻምበል አበበ ቢቂላን ድል በመድገም ታሪካዊ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ ይኖረናል በሚል የታዩብንን እጥረቶች ከወዲሁ በእቅድ አካተን የተሻለ ዝግጅት በማድረግ የሃገራችንን በጎ ገፅታ ለመገንባት ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል፤ እላለሁ፡፡ በ17ኛው የዶሃ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድል ከማጠናቀቅ በዘለለ በዓለም አትሌቲክስ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ተሳትፈናል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ በዚህ ወቅት በሁለት ዘርፎች ለሃገራችን እውቅና ሰጥቷል፡- የምንጊዜም ምርጥ አሰልጣኝ በማለት ዶ/ር ወ/መስቀል ኮስትሬን እና በረጅም ጊዜ አትሌትክስ አገልግሎት ላይ ለሰሩት ሥራ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጅሎ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የቬትራን ፒን ከዓለም አትሌትክስ ተሸልሟል፡፡  እንዲሁም የስኬታማ አትሌቶች መፍለቂያ በማለት ለቆጂ ከተማ ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ ይህ ለሃገራችን ትልቅ ድልና ጠብቀን ልናስቀጥለው የሚገባን ስኬት ነው፡፡

ክቡራት እና ክቡራን 

እንደ አንድ የስፖርት ማህበር ፌዴሬሽናችን ያልተቋረጠ የፋይናንስ ምንጭ ሊኖረው እንደሚገባ በማሰብ ቀደም ሲል የተጀመሩ ዘለቄታ ያላቸው የሃብት ማግኛ ስራዎቻችንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ እያስገነዘብኩ በበጀት ዓመቱ ከስፖንሰርሽፕ፣ ከዓለም አትሌቲክስ፣ ከአዲዳስ ኩባንያ፣ ከመንግስት ድጋፍ፣ ከፌዴሬሽኑ የውስጥ ገቢ እና ከሌሎች ምንጮች ከዘጠና ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ህግ እና ስርዓትን ተከትሎ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል፡፡ ስለሆነም በትንሿ ሜዳ ዙሪያ 137 ሱቆች ግንባታ ለመስራት ባሳለፍነው ዓመት በልዩ ልዩ  ምክንያት ቢዘገይም ስራውን የማሳለጥ ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በጉርድ ሾላ ዋናው ቢሯችን ጎን በሚገኘው ትርፍ ቦታ ግንባታ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርበን ከረጅም ጊዜ በኋላ ህዳር 11/2012 ዓ.ም 753.4 ካ.ሜ ከየካ ክፍለ ከተማ ከሊዝ ነፃ ቦታ ተረክበናል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታውን በጥራትና በፍጥነት ከሰራን የምንፈልገውን አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ተጨማሪ የሃብት ምንጭ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ በሌላ በኩል የግንኙነትንና የመረጃ ተደራሽነት ሥርአትን በመጠቀም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አትሌቲክስን የተመለከቱ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት በአግባቡ ያልፈጸምናቸውንና ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸውን ስራዎቻችንን በያዝነው በጀት ዓመት የእቅዳችን የትኩረት አቅጣጫ አድርገን መፈጸም እንደሚኖርብን ይታመናል፡፡ በንግግሬ ማጠቃለያ በበጀት ዓመቱ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ድጋፍ ላደረጉሉን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት፣ ለክልልና ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችና ስፖርት ኮሚሽን አመራሮችና ባለሙያዎች፣ በየደረጃው ለሚገኙ ክለቦች፣ አትሌቶች፣ የአትሌት ተወካዮች፣ አሰልጣኞች፣ ለስፖንሰራችን ሄኒከን ኢትዮጵያ የሶፊ ማልት ምርት ዘርፍ፣ ለፌዴሬሽኑ ሠራተኞችና ለስፖርት ጋዜጠኞች በሙሉ እንዲሁም የስራ እንቅስቃሴያችን ላይ ድጋፍ ላደረጉልን በሁሉም ሀገር ያሉት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎቻችንና የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽ የስፖርት ቤተሰብ፣ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውና በራሴ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡››

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ጉባዔው በሚከተሉት አጀንዳዎች ላይ በመነጋገር ላይ ይገኛል

  1. የክብር አባላትን አቅርቦ ማፀደቅ ፣
  2. የ22ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤን አይቶ ማፀደቅ፣
  3. የ2011 በጀት አመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ማፀደቅ፣
  4. የ2011 በጀት አመት የኦዲት ሪፖርት በማዳመጥና በመወያየት ማፀደቅ፣
  5. የ2011 በጀት አመት የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችን የሱፐርቪዥን ሪፖርትን ማዳመጥና ተሞክሮዎችን መውሰድ ፣
  6. የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብን፣ የግዥና ፋይናንስ የውስጥ መመሪያና የሠራተኞች አስተዳደር የውስጥ መመሪያን ተወያይቶ ማሻሻል ፣
  7. የ2012 በጀት አመት የሥራ እቅድና በጀትን ተወያይቶ ማፀደቅ ፣
  8. የ2012 በጀት ዓመት የውድድር ካላንደር ላይ መወያየትና ማፀደቅ ፣
  9. ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችና ክለቦች እንዲሁም ግለሰቦች የእውቅናና ማበረታቻ ሽልማት መስጠት፣
Similar Posts
Latest Posts from