የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እና ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የIAAF አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ አትሌቲክስ አሰልጣኞች ስልጠና ከዛሬ ግንቦት 28/2011 ዓ. ም ማለዳ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በኢት/ወጣ/ስፖ/አካዳሚ እየተሰጠ ይገኛል።

ከአሁን በፊት የIAAF እና የአገር ውስጥ ስልጠናዎችን ወስደው ውጤታማ የሆኑና በማሰልጠን ሙያ ላይ ለሚገኙ ከ20 ለማያንሱ አሰልጣኞች የሚሰጠው ስልጠና ከደ/አፍሪካ እና ከጀርመን በመጡ ታዋቂ የዘርፉ ባለሙያዎች ለቀጣይ 16 ቀናት በሁለት ምድብ የሚሰጥ ይሆናል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት ክብርት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትና መመሪያ አስተላልፋለች።

አያይዛም ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት መሠል ስልጠናዎችን ሲያመቻች የቆየ ቢሆንም የአሁኑ ስልጠና ፌዴሬሽኑ ከአለም አቀፉ ማህበር ጋር ባለው መልካም የስራ ግንኙነትና ትብብር የተገኘ ከመሆኑ አንፃር፣ በተለይም ለአጭር ርቀት፣ ለሜዳ ተግባራትና ለእርምጃ ውድድር አሰልጣኞች በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያ መሆኑን አመልክታለች።

አክላም ስልጠና የውድድርና ውጤት መሠረት በመሆኑ ከዚህ ስልጠና በኋላ ከአሰልጣኞች የሚጠበቅ ፍሬ እንደሚኖር አስገንዝባለች።

በመጨረሻም ሰልጣኞቹ መልካም የስልጠና ቆይታ እንዲሆንላቸው ተመኝታለች።

Similar Posts
Latest Posts from