ማክሰኞ ሚያዝያ 1/2011 ዓ. ም ምሽት ከ12:00 ሰዓት ጀምሮ የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ እኤአ ማርች 30/2019 በዴንማርክ – አርሁስ በ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ተካፍሎ በ5 ወርቅ፣ በ3 ብር፣ በ3 ነሃስ፣ በድምሩ በ11 ሜዳልያዎች ከዓለም 1ኛ ደረጃን በመያዝ በታላቅ ድል ወደ ሃገሩ ለተመለሰው የአትሌቲክስ ቡድናችን በታላቁ ቤተ መንግስት ከ1.4 ሚሊዮን ብር በላይ ለቡድኑ አባላት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ሰጥተዋል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ስመጥርና ታዋቂ አትሌቶች፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሚድያ አካላት ታድመዋል።

በዚህ ሂደት የቡድኑ መሪና የፌዴሬሽናችን ፕሬዝዳንት ክብርት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ከሣው የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ሚኒስትር በየተራ ድሉን የተመለከተ ንግግር አድርገዋል።

ከሽልማትና እውቅና አሰጣጡ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በየተራ ባሰሙት ንግግር ተደምሮ በጋራ መሥራት በአትሌቲክሱ ውስጥ እየታዬ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በፅናት፣ በትዕግስትና በንቃት የድል አድራጊነትን ሚስጥር አውቆ መጓዝ ዘለቄታ ላለው አሸናፊነት እንደሚያበቃ አስገንዝበዋል።

በዚህ አጋጣሚ የሪዮ ኦሎምፒክ ማራቶን ብር ሜዳልያ አሸናፊው አትሌት ፈይሣ ሌሊሣ ከተጋባዥ ታዋቂ አትሌቶች መካከል አንዱ ስለነበር ኮሚሽኑ፣ ኮሚቴውና ፌዴሬሽኑ በጋራ በክቡር ጠ/ሚ/ሩ እና በክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አማካይነት የ500,000.00 ብር ሽልማት አበርክተውለታል።

በመጨረሻም በጋራ ፎቶግራፍና በእራት መስተንግዶ መርኃ ግብሩ ተጠናቋል።

በስለሺ ብሥራት፣ የኢአፌ ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ፣

Similar Posts
Latest Posts from