ከዓለም አገር አቋራጭ ለተመለሰው የልኡካን ቡድናችን አቀባበልና ሽልማት ተደረገለት፤
በዴንማርክ አርሁስ ከተማ ለ43ኛ ጊዜ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በ5 ወርቅ፣ በ3 ብር እና በ3 ነሃስ በድምሩ በ11 ሜዳልያዎች ከዓለም 1ኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የአትሌቲክሰ ልኡካችን ዛሬ መጋቢት 24/2011 ዓ.ም. በአራራት ሆቴል ደማቅ የአቀባበልና የሽልማት መርሃ ግብር ተደርጎለታል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው የአባባ ጉንጉን ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት የእንኳን በድል ተመለሳችሁ ንግግር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መስራት የሚገባቸውን በመስራታቸው የቀደምቱ የአረንጓዴ ጎርፍ ውጤት መመለስን ማሳያ የሆነና በመደመር መንፈስ በጋራ የመጣ ድል በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ በቀጣይ በሚደረጉ አህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮች ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከፌዴሬሽኑ ጎን ቆሞ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም የኢ.ፌ.ድሪ. ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ለልኡካኑ አበባ ካበረከቱ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት የተገኘው ውጤት እንደ ሃገር የኮራንበትና ለቀጣይ ውድድሮች የበለጠ እንድንዘጋጅ የሚደርገን ሲሆን ኮሚሽኑም ባስፈላጊው መንገድ ሁሉ ፌዴሬሽኑን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን በመወከል አቃቢ ንዋይ ወ/ሮ ሄሮዳይት ዘለቀ በተገኘው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ከፌዴሬሽኑ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝዳት አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም የተመዘገበው ውጤት የሚያኩራራን ሳይሆን ለበለጠ ውጤት ወገባችንን ጠበቅ አድርገን እንድንሰራ ኃላፊነት የሰጠን ውጤት ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ለልኡካን ቡድናችን እንዳስመዘገቡት ውጤትና የስራ ሃላፊነት የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ስፖርት ኮሚሽን በጋራ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን ወርቅ ላስመዘገቡ 30,000.00 ብር፣ ብር ላስመዘገቡ 20,000.00 ብር፣ ነሃስ ላስመዘገቡ 10,000.00 ብር፣ ዲፕሎማ ላገኙ 6,000.00 ብር እና ለተሳታፊዎች የ3,000.00 ብር ለልኡካን ቡድኑም እንዳስመዘገቡት ውጤት ኃላፊነት የገንዘብ ሽልማት ሲበረከትላቸው በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑ ብር 650,000.00 ብር ለሽልማት ወጪ አድርጓል፡፡

 

Similar Posts
Latest Posts from