በናይጀሪያ ሲካሄድ በቆየው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈለው የልኡካን ቡድናችን ተሸለመ፤

በናይጀሪያ – አሳባ ከተማ ለ21ኛ ጊዜ ከሐምሌ 25 – 29/2010 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየው 21ኛው የአፍሪካ አዋቂዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የልኡካን ቡድናችን በ2 ወርቅ፣ በ3 ብርና በ5 ነሃስ በድምሩ በ10 ሜዳልያዎች ከተሳታፊ 32 የአፍሪካ ሃገራት መካከል 5ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ሃገሩ የተመለሰ ሲሆን ዛሬ አሮብ ነሃሴ 2/2010 ዓ. ም. ከማለዳው 3፡00 ሰዓት ላይ የአቀባበልና የማበረታቻ ሽልማት ሥነ ስርዓት ተካሂዶለታል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ክቡር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላት፣ ሰራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው የስፖርት ሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ከአበባ አሰጣጥ ፕሮግራም በኋላ እንደተናገረው በቡድኑ ጠንካራ ዲሲፕሊንና ከውድድሩ በርካታ ነገሮች የተቀሰሙ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑንና ከውጤት አኳያም ክፍተቶችን በአግባቡ በማየት ለአለም ሻምፒዮናና ለቶኪዮው የኦሎምፒክ ጨዋታ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ምን ሊሰራ እንደሚገባው በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያመላከተ ውድድር መሆኑን ጠቅሶ አባላቱን እንኳን በሰላም ወደ ሃገራችሁ መጣችሁ ብሏል፡፡

በመቀጠልም ለቡድኑ አባላት የተዘጋጀው እና ከ700,000 ብር በላይ የሚሆነው የማበረታቻ ሽልማት ገንዘብ የተበረከተ ሲሆን ከማበረታቻ ሽልማቱ በኋላ የቡድኑ መሪና የኢአፌ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አድማሱ ሳጂ አጠቃላይ ስለጉዟቸው፣ ስላጋጠሟቸው ችግሮች፣ ስለመፍትሄዎቹና ስለውድድሩ ሁኔታ በዝርዝር በስፍራው ለነበሩ አካላት አብራርተዋል፡፡

ዘገባ፡- ስለሺ ብሥራት – በኢአፌ የኮሙኒኬሽን ከፍ/ኤክስፐርት፤ ነሃሴ 2/2010 ዓ. ም. አዲስ አበባ፤

 

Similar Posts
Latest Posts from