ከሰዓት በፊት በመክፈቻው በተደረገ የ3000 ሜ. መሰናክል የሴቶች ውድድር ከምድቧ 2ኛ ሆና አገሬ በላቸው በ9፡59.95 የራሷን ወቅታዊ ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ፣ በሌላኛው ምድብ የነበረችው እታለማሁ ስንታዬሁ ደግሞ የግሏን ምርጥ ሰዓት 9፡52.92 አስመዝግባ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል፡፡

በ1500 ሜ. ወንዶች ብርሃኑ ሶርሳ ከምድቡ 2ኛ ሆኖ በ3፡44.92፣ ሳሙኤል ተፈራ ደግሞ 3፡44.08 በሆነ ጊዜ ከምድቡ 1ኛ ሆነው አልፈዋል፡፡

በ800 ሜ. ሴቶች አገራችንን ሁለት እንስቶች የወከሉ ሲሆን ፍሬወይኒ ኃይሉ 2፡08.27፣ ድርቤ ወልተጂ ደግሞ 2፡05.19  በሆነ ጊዜ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በተካሄዱ ውድድሮች በተለይ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የአለምን ሚኒማ በማሟላት በ400 ሜ. ሴቶች 2 አትሌቶችን ማሰለፍ ችለናል፡፡ በዚህ ውድድር ፍሬህይወት ወንዴ ከምድቧ 4ኛ ደረጃ ብትይዝም ባስመዘገበችው ሰዓት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች፡፡ በዚህ ርቀት በሌላኛው ምድብ የነበረችው ማህሌት ፍቅሬ አለም አቀፍ ልምድ ብታገኝም ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለችም፡፡

ከቀኑ 11፡40 ላይ በተካሄደው የሴቶች 5000 ሜ. ፍጻሜ ውድድር እጅጋዬሁ ታዬ 15፡30. 87 በሆነ ጊዜ 2ኛ ሆና የመጀመሪያውን የብር ሜዳልያ ለራሷና ለሃገሯ ማስገኘት ችላለች፡፡ እሷን ተከትላ በ15፡34.01 ሰዓት የገባችው የሃገሯ ልጅ ግርማዊት ገ/እግዚአብሄር 3ኛ የወጣች ሲሆን ለራሷና ለሃገሯ የመጀመሪያ የሆነውን ነሃስ ሜዳልያ ማስገኘት ችላለች፡፡ ለአለም አቀፍ ውድድሮች ብዙም ልምድ ያለነበራቸው ቢሆንም ወርቁ በሌሎች የተወሰደው በጥቂት ማይክሮ ሰከንዶች መሆኑ አትሌቶቻችንን አስቆጭቷል፡፡

በትላንትናው እለት ጠንካራ ፉክክር የተደረገበትና በእድሜ ትንሹ በሆነው ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከፍተኛ ጥረት በ10000 ሜ. ወንዶች 27፡48.41 በሆነ ጊዜ በመግባት 2ኛው የነሃስ ሜዳልያ ሲገኝ ከእርሱ ጋር የነበረው አትሌት ኦሊቃ አዱኛ በ28፡39.67 በሆነ ጊዜ 5ኛ ሆኖ ዲፕሎማ ማግኘት ችሏል፡፡

በመጀመሪያው ቀን ውሎ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት ኢትዮጵያ ከኬንያና ደቡብ አፍሪካ ቀጥላ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ውድድሮቹ ዛሬም ሐምሌ 4/2010 ዓ.ም. ቀጥለዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በአጭር ርቀቶች ሃገራችን በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሰለፈች ቢሆንም ማለዳ ላይ በተካሄደው የ400 ሜ ወንዶች ማጣሪያ ላይ አብዱራህማን አብዶ ማለፍ አልቻለም፤ መልካሙ አሰፋ ደግሞ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡

ከሰዓት በኋላ ከምሽቱ 11፡10 ሰዓት ላይ የሴቶች 800 ሜ. ግማሽ ፍጻሜ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ፍሬወይኒ ኃይሉና ድርቤ ወልተጂ ይሰለፋሉ፡፡

ከምሽቱ 12፡25 ሰዓት ላይ ደግሞ የሴቶች 400 ሜ. ግማሽ ፍጻሜ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ፍሬህይወት ወንዴ ትሰለፋለች፡፡ 12፡55 ሰዓት  ላይ ደግሞ በጉጉት የሚጠበቀው የሴቶች 3000 ሜ. ቀጥታ ውድድር ፍጻሜ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ መሰሉ በርሄ እና ጽጌ ገ/ሰላማ ተሰላፊዎች ናቸው፡፡

ድል ለአትሌቶቻችን!!

ስለሺ ብሥራት የኢአፌ ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ – ከፊንላንድ ታምፐሬ ሐምሌ 4/2010 ዓ.ም.

Similar Posts
Latest Posts from